የምጥ ምልክቶች

በምጥና በወሊድ ጊዜ ማህፀን በተደጋጋሚ የመኮማተርና የመላላት ሂደት ያደርጋል፡፡ ይህ ሂደት የማህፀን በር እንዲሳሳና እንዲከፈት በማድረግ ልጁ እንዲወጣ ሰውነትሽን ያዘጋጃል። ማንም ሴት ስለመወለድ ስታሰብ የምትፈራው ምጥ ነው፡፡ የሁሉም ሰው  ምጥ ቢለያይም የምጥ ህመም ከምንም ጋር የሚወዳደር አደለም፡፡ ስለምጥ ማወቅ እንድትፈሪ ሳይሆን እንድትዘጋጂ ሊያረግሽ ይገባል፡፡

ምጥ ሁለት አይነት ሲሆን የመጀመሪያው የውሸት ምጥ ወይም በተለሞዶ መንገድ ጠራጊው ሲባል ሁለተኛው ደግሞ መውለጃሽ ሲደርስ የሚጀምርሽ እውነተኛ ምጥ ነው፡፡ እርግዝና የሚከሰትበት ትክክለኛ ጊዜ ስለማይታወቅና የወሊድ ቀንሽ ሁለት ሳምንት ወደ ፊት ወይም ወደ ኃላ  ሊል ስለሚችል ምጥ መቼ ሊጀምርሽ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አትችይም።

ትክክለኛው ምጥ ከመጀመሩ ሁለት ሳምንታትን አስቀድሞ ማህፀንሽ መፍታታት ይጀምራል፡፡ ይህ ለዋናው ምጥ ቅድመ ዝግጅት ነው። ይህ የማህፀን  መፍታታት ለብዙ ሴቶች ባያስታውቅም ለአንዳንድ ሴቶች ልክ የወር አበባ ሲመጣ የሚሰማን አይነት የሆድ ቁርጠት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ይህንን የሆድ ቁርጠትም ነው መንገድ ጠራጊ የምንለው፤ የልጅሽን መምጣት እያበሰረ ነውና። እውነተኛ  ምጥን ከውሸተኛው ምጥ መለየት ትክክለኛው ምጥሽ ሲመጣ ባፋጣኝ ወደ ሃኪም ቤት እንድትሄጂ ይረዳሻል፡፡

የእውነተኛ ምጥ ምልክቶች

 • የእንሽርት ውሀ መፍስስ ዋነኛው ምልክት ነው፡፡ የእንሽርት ውሀ ልጅሽን ከቦ ከአደጋ የሚጠብቀው ፈሳሽ ነው፡፡ ልጅሽ እንዲወጣ መፍስስ አለበት፡፡ በአብዛኛው ጊዜ በምጥ ሰአት ቢሆንም የሚፈሰው አንዳንድ ሴቶች ላይ ምጥ መቶ (ማህፀን ተከፍቶ) የእንሽርት ውሀ ላይፈስ ይችላል። የእንሽርት ውሀ ፈሶ ደግሞ ማህፀን ያለመከፈትም እድል አለው። 

ቀድሞ የእንሽርት ውሀ ፈሶ ምጥ ካልጀመረሽ የምጥ መርፌ ሲሰጥ ምጥሽ መቶ የእንሽርት ውሀሽ ካልፈሰሰ ደግሞ አዋላጅሽ የእንሽርት ውሀው እንዲፈስ ታደርጋለች። ይህ የሚሆነው በአንድ በኩል ምጥ ከመጣ (ማህፀን ከተከፈተ) ልጁን ገፍተሸ ለማውጣት የእንሽርት ውሀሽ መፍሰስ ስላለበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የእንሽርት ውሀሽ ከፈሰሰ ልጁ እንዳይታፈን የምጥ መርፌ ተሰቶሽ ማማጥ መጀመር ስላለብሽ ነው። የእንሽርት ውሀሽ ከፈሰሰ ከ12-24 ሰአት ውስጥ መውለድ አለብሽ ያለበለዝያ ልጅሽ ኢንፌክሽን ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

 • የሆድ ቁርጠት ሌላው የምጥ ምልክት ነው። በመጠንም በፍጥነትም ከመንገድ ጠራጊው ይጨምራል (ለበለጠ መረጃ የምጥ ደረጃዎችን አንብቢ)። እያንዳንዱ ቁርጠት ለረዥም ጊዜ የሚቆይና በጣም የሚያም ሲሆን ቶሎ ቶሎ የሚመላለስ ይሆናል ምንም በማድረግ ሊቀል አይችልም። ህመሙም ከጀርባሽ አንስቶ እምብርትሽ ድረስ የሚዞር ህመም ነው፡፡
 • የማህፀንሽ በር መስፋት ይጀምራል ከዜሮ ተነስቶ እሰከ 10 ሴንቲ ሜትር ድረስ ይሰፋል።

መንገድ ጠራጊ (የውሸት ምጥ) ምልክቶች

 • በወር አበባ ጊዜ የሚሰማሽን አይነት የሆድ ቁርጠት ሊሰማሽ ይችላል፡፡ የሚያምሽን ቦታ ለይተሸ የማወቅ እድልሽም አናሳ ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ገላን በመታጠብና እረፍት በማድረግ ስሜቱን ማጥፋት ይቻላል፡፡ ያለሽበትን ሁኔታ በመቀየር በመቀመጥ፣ በመተኛት ወይም በመራመድ እንዲቀልሽ ማድረግ ትችያለሽ፡፡ ይህ ስሜት በተወሰነ የጊዜ ልዩነት የሚከሰት፤ ሲከሰት የማቆይና እንደ እውነተኛ ምጥ የማያም ነው፡፡
 • ሆድሽ ከነበረበት ቦታ ለቆ ወደታች ይወርዳል፡፡ ይህም የሽንት ቧንቧሽ ላይ ጫና ስለሚያበዛ ከተለመደው በበለጠ ቶሎ ቶሎ ሊያሸናሽ ይችላል፡፡
 • በእርግዝና ሰአት የማህፀንሽን በር  ዘግቶ የሚቀመጠው ዝልግልግ ፈሳሽ መፍሰስ ሌላኛው የመንገድ መጥረጊያ ምልክት ነው፡፡ ይህ ፈሳሽ አንዴ ወይም ቀስ እያለ ቀን በቀን ከተለመደው የሴትነት ፍሳሽሸ ጋር ሊወጣ ይችላል፡፡ የተዝለገለገና ቀይ ወይም ቡኒ የሆነ ቀለም ይኖረዋል።

የምጥ ሂደት

ወሊድ ምጥን ጨምሮ ሶስት ዋና ዋና ደረጃዎች አሉት።
ምጥ
ምጥ በራሱ ሶስት ደረጃዎች ሲኖሩት የማህፀንሽ በር ልጁን ለማስወጣት የሚዘጋጅበት ደረጃ ነው።

ቅድመ ምጥ – ደረጃ አንድ
 • የማህፀን በር ከ0 እስከ 4 ሴንቲ ሜትር ይከፍታል
 • የቁርጠት ስሜት እሰከ 30 ስከንድ ሲረዝም ከ5 እሰከ 30 ደቂቃ እየቆየ ይመጣል
 • የጀርባ ህመም፣ ጭንቀት፣ ወደታች የማለትና ትግስት የማጣት ስሜቶች ይኖራሉ 
 • በዚህ የምጥ ደረጃ ላይ ህመሙ ብዙ ስለማይቆይና ጠንካራ ስላልሆነ እረፍት ማረግ ትችያለሽ፡፡ ከበላሽ ብዙ ሰአታት ከሆነሽ ቀለል ያሉና በፍጥነት የሚፈጩ ምግቦችን መመገብ ይኖርብሻል፡፡ እረፍት ማረጉና ምግብ መውሰዱ በወሊድ ጊዜ የሚያስፈልግሽን ጉልበት እንዲኖርሽ ያደርጋል፡፡
 • እረፍት  የማረግ ስሜት ከሌለሽ መንቀሳቀስ ምጡን ሊያቀልልሽ ይችላል፡፡
 • በዝግታና በጥልቀት መተንፈስ እንዳትረሺ፡፡
ዋናው ምጥ – ደረጃ ሁለት
 • የማህፀንሽ በር ከ5 እስከ 8 ሴንቲ ሜትር ይከፈታል
 • የቁርጠቱ ስሜት ከ45 እስከ 60 ሰከንድ ሲቆይ በየ3 ወይ 5 ደቂቃው ይከሰታል
 • የምጡ መጠንከርና ቶሎ ቶሎ መሰማት የመውለጃሽን መቃረብ ስለሚያሳይ የደስታን ስሜት በመፍጠር ትኩረት እንድትሰጪ ያደርግሻል
 • ሊጨንቅሽ እረፍት ልታጪና ሰው ካጠገብሽ እንዲሆን ልትፈልጊ ትችያለሽ
 • እሰከቻልሽ ድረስ እንቅስቃሴ እንድታረጊ ቢመከርም ካልቻልሽና ከተኛሽ ግን የአተኛኘት መንገድሽን ቶሎ ቶሎ መቀየር ይኖርብሻል፡፡
 • እያንዳንዱ የምጥ ስሜት ሲያልፍ ራስሽን ማረጋጋት እንጂ ሰለሚቀጥለው ህመም ማሰብ የለብሽም፡፡
መሽጋገራያ ምጥ – ደረጃ ሶስት
 • የማህፀን በር ከ8 እስከ 10 ሴንት ሜትር ይከፈታል
 • የቁርጠት ስሜት ከ60 እስከ 90 ሰከንድ ሲቆይ በ2 ወይም 3 ደቂቃ መሀል ይከሰታል
 • የማቅለሽለሽ፣ የማስታወክ፣ የእግር መቆርጠምና መንቀጥቀጥ፣ ስቅታ፣ ማቃር፣ የእግር መቀዝቀዝ፣ የሰውነት መጋልና ማላብ፣ የማያቋርጥ የወገብ ህመም፣ ወደታች የማለት ስሜትና ልጅሽን ግፊ ግፊ የሚሉ ስሜቶች የተለመዱ ናቸው
 • ሁሉንም ረስተሸ ምጡ ላይ ታተኩሪያለሽ
 • ሀኪም እንድትገፊ አስኪነግርሽ ድረስ መግፋት የለብሽም፡፡
 • ከሚያዋልድሽ ወይም አብሮሽ ከገባ ቤተሰብ ጋር መተያየትና እንዳሉልሽ ማሰብ ህመሙ ላይ እንዳታተኩሪ ይረዳሻል።
የልጅሽ መወለድ
 • የማህፀን በር 10 ሴንት ሜትር ይከፈታል
 • የቁርጠት ስሜት ከ45 እስከ 90 ሰከንድ ሲቆይ በየ2 ወይም 5 ደቂቃ መሀል ይከሰታል
 • ለመውለድ ዝግጁ ስለሆንሽ መግፋት ትጀምሪያለሽ
 • በያንዳንዱ የምጥ ህመም፤ በያንዳንዱ ግፊት ልጅሽ አንድ እርምጃ ለመወለድ ይቀርባል
 • ልጅሽ በትክክለኛው መንገድ ከመጣ በመጀመርያ ጭንቅላቱ ይሆናል የሚወጣው እትብቱ የልጅሽ አንገት ላይ ተጠምጥሞ ከሆነና ሳይቆረጥ ሙሉ አካሉ ከወጣ ልጅሽ ትንፋሽ ሊያጥረው ስለሚችል ጭንቅላቱ እንደወጣ መግፋት ማቆም ይኖርብሻል፡፡ የተቀረው ሰውነቱ ጭንቅላቱን ተከትሎ በራሱ መንገድ ይወጣል፡፡
 • የልጁ ጭንቅላት ሊወጣ ሲል ከፍተኛ የመግፋት ስሜት እንዲሁም የመጫን ስሜት ይኖረዋል፡፡ ልክ ጭንቅላቱ ሲወጣ አንዳች ነገር ሰውነትሽን የሰነጣጠቀው ያህል ቢሰማሽ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ሲሆን የምጥ ህመሙ እየቀነስ ይመጣል።
 • ልጅሽ ሙሉ ለሙሉ እንደወጣ አዋላጅሽ ደረትሽ ላይ እንዲተኛ ታረጋለች። ይህ በሁለታችሁ መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠንከሩም በላይ ክትባት እሰኪወጋ ድረስ ያንቺ ሙቀት ከሳምባ ምች ይከላከለዋል፡፡
 • ሰውነቱ ነጭ ቢሆንና ደም ብታይበት እንዳትረበሺ ሲታጠብ የሚለቁ ናቸው፡፡
 • ልጅሽን መግፋት መጀመርያ ላይ ሊያስቸግርሽ ቢችልም ሲደጋገም የምትለምጂው ይሆናል፡፡ የምጥ ህመሙ ሲጀምርሽ ጠለቅ ያለ አየር በመውሰድ ህመሙ እሰኪያቆም ድረስ መግፋት ይኖርብሻል፡፡ የሚቀጥለው ህመም እስኪመጣ እረፍት አድርጊ። የምጥ ህመም ከፍተኛ መሆኑ የታወቀ ነውና መጮህ ካሰኘሽ ለመጮህ አትፍሪ ግን ሀይልሽን ላለመጨረስ ሞክሪ።
የእንግዴ ልጅ መውጣት
 • ልጅሽ ከተወለደች በኃላ የእንግዴ ልጁ ከማህፀንሽ ግድግዳ በመላቀቅ ወደ ውጪ ይወጣል።
 • ቀለል ያለ የሆድ ቁርጠት በዛ ያለ ደም መፍሰስ ይኖራል፡፡
 • ልጅሽ እንደተወለደች ጡት ማጥባት አንደኛው ጥቅሙ ጡት በምታጠቢበት ጊዜ የሚመነጩ ሆርሞኖች ማህፀንሽ እንዲኮማተርና የእንግዴ ልጁ እንዲወጣ ያደርጋሉ፡፡ የእንግዴ ልጁ ከወጣ በኃላም ብዙ ደም እንዳይፈስሽ ይረዳል፡፡ አዋላጅሽ ሆድሽን በማሸት አላስፈላጊ ፈሳሾች ከማህፀንሽ እንዲወጡ ታረጋለች ያም ህመምን ይፈጥራል፡፡
 • ከወሊድ በኃላ ራስሽንና ልጅሽን እንዴት መንከባከብ እንዳለብሽ ለማወቅ የአራስ ልጅ እንክብካቤን እና ድህረ ወሊድ የሚሉትን መረጃዎች አንብቢ
እነዚህ ደረጃዎች በምጥ የሚወልዱ ሴቶችን ያማከለ ነው ለበለጠ መረጃ የመውለጃ መንገዶችን ማንበብ ይኖርብሻል፡፡

የወሊድ መንገድች

በምጥ መውለድ
አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር በምጥ መውለድ ለልጅሽም ላንቺም ጤንነት ወሳኝ ነው፡፡ በምጥ መውለድ ተፈጥሮአዊ ሂደት ስለሆነ በአብዛኛው ችግር አያጋጥምሽም፡ ፡እንዳንቺና የልጅሽ የጤና ሁኔታ ግን አንዳንድ የህክምና ውሳኔዎች ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ የምጥ መርፌ መወጋት ነው። በምጥ ሰዓት የልጅሽ ልብ ምት ከቀነስ፤ ማህፀንሽ ተከፍቶ የምጥ ስሜት ካልተሰማሽ ወይም የእንሽርት ውሃሽ ፈሶ የምጥ ስሜት ካልተሰማሽ የምጥ መርፌ ትወጊያለሽ፡፡ ይህ የምጥ መርፌ ምጥሽ የተፋጠነ እንዲሆን ይረዳሻል እንጂ ምንም ጉዳት አያደርስም፡፡ ሌላኛው የህክምና ውሳኔ ስቲች ማረግ ነው። የውጪኛው የብልት ክፍተት ልጁን ለማስወጣት በቂ ካልሆነ ከብልትሽ ቀዳዳ ወደጎን ወይም ወደታች በመቅደድ እንዲሰፋ ይደረጋል፡፡ ማደንዘዣ ስለሚሰጥሽ ሲቀደድ ህመም አይኖረውም። ከወለድሽ በኌላ መልሶ ይሰፋል፡፡ ከወሊድ  በኃላ ባሉት ተከታታይ ቀናት በደንብ ራሰሽን ከጠበቅሽ በቀላሉ የሚድን ቁስል ነው (ለተጨማሪ መረጃ ከወሊድ በኃላ የሚለውን ክፍል አንብቢ)። ልጅሽ ለወሊድ በሚመች መንገድ ካልተቀመጠ፣ የልጅሽ ጤንነት አደጋ ላይ ከሆነና ቶሎ መወለድ ካለበት፣ እንዲሁም አንቺ የመግፋት አቅም ከሌለሽ ጭንቅላት ላይ በሚደረግ መሳርያ ልጁ ተጎትቶ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ይህን ለማድረግ አስፈላጊ ከሆነ ስቲች መሰራት ሊኖርብሽ ይችላል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን አይነት ያልተጠበቁ የጤና እክሎች  በሰላም ለመወጣት ሁልጊዜም በህክምና ተቋም መውለድ ተመራጭ ነው፡፡
በምጥ መዉለድ ጥቅሙ
በምጥ መዉለድ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል
 • አጭር የሆስፒታል ቆይታ
 • የደም መፍሰስ፣ ጠባሳና ኢንፌክሽን አያመጣም
 • በትክክለኛዉ ጊዜ ጡት ማጥባት ትጀምሪያለሽ
 • በምጥ ጊዜ ልጅሽ የሚወጣበት የማህፀንና የብልት ቀዳዳ ጠባብ ስለሆነ ሳንባ ዉስጥ ያሉት ፈሳሾች ተጨምቀዉ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ ይህም ልጅሽ በሳንባ ምች እንዳይመታ ይረዳዋል፡፡
 • በምጥ የሚወለድ ልጅ በሴት ብልት ዉስጥ ለሚገኙ ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ተጋላጭ ነዉ፡፡ ይህ በሽታ የመከላከል አቅሙን ይጨምራል፡፡
 • ለሚቀጥለዉ እርግዝናና ወሊድ ምንም አይነት ተጽእኖ አይኖረዉም፡፡

በምጥ መዉለድ ጉዳቱ
 • የምጥ ህመም
 • የብልት የውጨኛው ክፍል መሰነጣጠቅ (ስቲች መሰራት)።
 • አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ሽንትና ሰገራ መቆጣጠር ሊከብድ ይችላል።

በቀዶ ጥገና መውለድ
በቀዶ ጥገና ከሆነ የምትወልጂው ሆድሽ ተከፍቶ ልጅሽ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ ሁልጊዜም በምጥ እንድትወልጂ ይደረጋል፡፡
በቀዶ ጥገና እንድትወልጂ የሚያስገድዱ ምክንያቶች
 • ልጅሽ መጠኑ ትልቅ ከሆነ
 • መውለጃሽ ሲደርስ ልጅሽ ጭንቅላቱ ወደታች መሆን ሲገባው እግሩ፣እጁ ወይ ሌላ አካላቱ ወደታች ከሆነ
 • አንቺ ወይም ልጅሽ የጤና እክል ካለባችሁ፡፡ ለምሳሌ አንቺ የደም ግፊትሽ ከፍተኛ ከሆነ፣ የአባላዘር በሽታ ካለብሽ፣ ማማጥ ካልቻልሽ፤ ልጅሽ የኦክስጅን እጥረት ካጋጠመው ወይም የልብ ምቱ ከቀነስ እንዲሁም መንቀሳቀስ ካቆመ
 • የእንግዴ ልጅ ወይም እትብቱ ላይ ችግር ካለ
 • ምጥሽ በተገቢው ፍጥነት እየሄደ ካልሆነ
 • ከአንድ በላይ ልጅ አርግዘሽ ከሆነ
 • የመውለጃ ቀንሽ ካለፈ
አንዳንዶቹ ምክንያቶች በእርግዝና ሰዓት ስለሚታወቁ ለቀዶ ጥገና ዝግጁ እንድትሆኚ ይነገርሻል፡፡ ሌሎቹ ምልክቶች ምጥ ይዞሽ ከገባሽ በኋላ ሊከሰቱና ቀዶ ጥገና መደረግሽ ድንገተኛ ሊሆን ይችላል፡፡
በቀዶ ጥገና መዉለድ ጉዳቱ
በቀዶ ጥገና መዉለድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይብሳል፡፡ ለዛም ነዉ ግዴታ ካልሆነ የማይመረጠዉ፡፡ በቀዶ ጥገና መውለድ ከሚያመጣቸው ችግሮች መሀል
 • የደም መፍሰስ
 • ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር ኢንፌክሽን እና የደም መርጋት
 • ረዥም የሆስፒታል ቆይታ
 • ህፃናትን ለመተንፈሻ አካልና ለሳምባ ምች ያጋልጣል
 • የኦፕራሲዮን ቁስል ቶሎ አይድንም ለማገገም እስከ ሁለት ወር ድረስ ሊፈጅ ይችላል
 • ልጅሽን ቶሎ ጡት እንዳታጠቢና ቅርበት እንዳትፈጥሪ ያረጋል
 • አንዴ በኦፕራሲዮን መውለድ ከጀመርሽ ድጋሚ በምጥ የመዉለድ እድልሽ እጅግ የጠበበ ነዉ
 • በቀጣይ እርግዝናሽ ላይ የተሰፋዉ ማህፀንሽ ሊቀደድና የእንግዴ ልጁን ሊጎዳዉ ይችላል፡፡
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ