ቁልፍ መልእክቶች

ልጅሽ 6 ወር ሲሆነው ተጨማሪ ምግብ ጀምሪለት፡፡ ለስለስ ያለ ገንፎ በቀን ከ2-3 ጊዜ መግቢው፡፡ ልጅሽ ጤነኛና ጠንካራ ሆኖ ያድጋል፡፡

ገንፎ ከተለያዩ የእህልና የጥራጥሬ ዓይነቶች ሊዘጋጅ ይችላል፡፡
 • ስታዘጋጂ 3 እጅ ከእህልና 1 እጅ ከጥራጥሬ ሆኖ በጣትሽ መመገብ እንድትችይ ሆኖ ይወፍር፡፡
 • የልጁ ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የመዋጥ ችሎታውን እያገናዘብሽ ገንፎውን ማወፈር፡፡
 • የልጁ ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የመዋጥ ችሎታውን ያገናዝቡ ገንፎውን ያወፍሩት፡፡
 • ገንፎውን ለማዘጋጀት ከተቻለ በውሃ ፋንታ ወተት ተጠቀሚ፡፡
 • ከተቅማጥና ከሌሎች በሽታዎች ለመከላከል ለልጅሽ የምታዘጋጂውና የምትመግቢው ምግብ በንጽህና የተዘጋጀና የተቀመጠ መሆን አለበት፡፡

ልጅሽ ጠንካራ እንድትሆን ሁለት ዓመትና ከዚያም በላይ እስኪሆናት ድረስ ጡት ማጥባት ቀጥይ፡፡ ባሰኛት ጊዜ ሁሉ ቀንም ሆነ ሌሊት በቀን ቢያንስ ስምንት ጊዜ አጥቢያት፡፡

ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ላሉ ሕፃናት የጡት ወተት ተፈላጊ የምግብ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡

ልጅሽ የሚመገበው ገንፎ የዳበረ እንዲሆን ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በመጨመር አበልፅጊው፡፡ ምሳሌ ቅቤ፣ ዘይት፣ ለውዝ፣ ስጋ፣ እንቁላል፣ አትክልትና ፍራፍሬ መደባለቅ ለልጅሽ ዕድገትና ጥንካሬ ጠቃሚ ነው፡፡

 • ከስድስት ወር ጀምሮ ከጡት ወተት በተጨማሪ ለልጅሽ ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የተጨመረበት የበለጸገ ምግብ መግቢ፡፡
 • በየጊዜው የተለያዩ ምግቦችን ለመመገብ ምክሪ፡፡
 • ገንፎውን ለማበልጸግ የሚጨምሩትን የምግብ ዓይነት ሕፃኑ በቀላሉ መዋጥ እንዲችል ይድቀቅ፡፡
 • የላም ወተት መስጠት ትችያለሽ፤ ሆኖም ተጨማሪ ምግቡን መተካት የለበትም፡፡
 • በሚዘጋጀው ተጨማሪ ምግብ ውስጥ ሁሉ ዘይት ወይም ቅቤ ጨምሪ፡፡
 • የእንስሳ ውጤቶች (ስጋ፣ ጉበት፣ አሣ፣ እንቁላል) መስጠት ለልጅሽ ጤንነትና ዕድገት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
 • ቢጫ መልክ ያላቸው ፍራፍሬዎችን (ማንጎ፣ ፓፓያ) እና አትክልቶች (ካሮት) ጥሩ የቫይታሚን ኤ ምንጭ ናቸው፡፡
 • ጥቁር አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎች (ጎመን) እና ጥራጥሬዎች እንደ አይረን /ብረት/ ላሉ ንጥረ ነገሮች ምንጭ ናቸው፡፡

ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ወር ያሉ ሕፃናት ዕድገታቸው የተስተካከለ እንዲሆን በቀን ከሁለት አስከ ሦስት ጊዜ ከሚሰጠው በተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ከበለፀገው ገንፎ በተጨማሪ አንዴ ወይም ሁለቴ መክሰስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

 • ሕፃናት ጨጓራቸው ትንሽ በመሆኑ በአንዴ ብዙ መመገብ አይችሉም፡፡ ስለዚህ በተደጋጋሚ ትንሽ ትንሽ ቶሎ ቶሎ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
 • ስምንት ወር የሞላው ሕፃን በጣቶቹ እያነሳ ሊመገብ ስለሚችል በትናንሹ የተቆራረጠ የበሰለ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ ሌሎች ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ትኩስና የተጠበሰ ዳቦ፣ የተቀቀለ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ቂጣና የመሳሰሉትን መስጠት ያስፈልጋል፡፡
 • ገንፎውን ለማበልጸግ የሚጨምሩትን የምግብ ዓይነት ሕፃኑ በቀላሉ መዋጥ እንዲችል ይድቀቅ፡፡
 • እነኚህ በትናንሽ የተቆራረጡ ምግቦች በየቀኑ አንዴ ወይም ሁለቴ በመክሰስ መልክ መስጠት ይመከራል፡፡
 • ተቅማጥና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተዘጋጀውን ምግብ በንጽህናና በጥንቃቄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡

ከአስራ ሁለት እስከ ሀያ አራት ወር ዕድሜ ለሆናቸው ልጆች በቀን ቢያንስ ከ3 – 4 ጊዜ ያህል ቤተሰብ ከሚመከበው ምግብ መመገብና አንዴ ወይም ሁለቴ መክሰስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ጤነኛና ጠንካራ እንዲሆን ይረዳል፡፡

 • ለልጁ የሚሰጠው የቤተሰብ ምግብ በተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የበለጸገ መሆን ይገባዋል፡፡
 • ሕፃናት ጨጓራቸው ትንሽ በመሆኑ በአንዴ ብዙ መመገብ አይችሉም፡፤ ስለዚህ በተደጋጋሚ ትንሽ ትንሽ ቶሎ ቶሎ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
 • መክሰስ በተደጋጋሚ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይህም በትናንሹ የተቆራረጠ የበሰለ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሙዝ ሌሎች ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ትኩስና የተጠበሰ ዳቦ፣ የተቀቀለ ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ቂጣና የመሳሰሉት ሊሆን ይችላል፡፡
 • ተቅማጥና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የተዘጋጀውን ምግብ በንጽህናና በጥንቃቄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
 • ልጅሽ ዕድሜው በጨመረ ቁጥር የምትሰጭውን የምግብ መጠን በርከት ማድረግ ለዕድገት የሚያስፈልገውን በቂ የምግብ ኃይል እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡

ልጅሽ የተስተካከለ ዕድገት እንዲኖራት በትዕግስት እያጫወትሽ ምግቡን አስጨርሺ፡፡

 • ሕፃኗ ከጡት ወተት ውጭ ምግብ ስትጀምር እንግዳ ስለሚሆንባት እስክትለምደው ታገሽ፡፡ እያባበልሽና እያጫወትሽ መግቢያት፡፡
 • የምትበላው የምግብ መጠን እንዲታወቅ የራሷ ሳህን ይኑራት፡፡
 • ልጅን አስገድዶ መመገብ ምግብ እንዲጠላ ያደርጋል፡፡
 • ሕፃናት ምግባቸውን በራሳቸው በልተው መጨረስ ስለማይችሉ እያጎረሽ ማስጨረስ ያስፈልጋል፡፡
 • ከፍ ላሉ ልጆችም ቢሆን የተሰጣቸውን ምግብ መጨረሳቸውን መከታተል ያስፈልጋል፡፡

ልጅሽ በፍጥነት እንዲያገግም በህመም ወቅት ጡትና ተጨማሪ ምግብ ቶሎ ቶሎ ስጪ፡፡

 • በህመም ወቅት የፈሳሽና የምግብ አስፈላጊነት በጣም ይጨምራል፡፡
 • በህመም ወቅት የምግብ ፍላጎት ስለሚቀንስ ጊዜ ወስደሽ በትዕግስት በትንሽ በትንሹ ቶሎ ቶሎ ልጅሽን መግቢ፡፡
 • በተለይ ልጅሽ የሚወደው ምግብ ካለ ያንን እንዲመገብ ማበረታታት ይጠቅማል፡፡
 • ልጅሽ ጥንካሬውን እንዳያጣና ክብደቱም እንዳይቀንስ በህመም ወቅት የጡት ወተትም ሆነ ተጨማሪ ምግብ መስጠትዎን መቀጠል ይኖርብሻል፡፡
 • ልጅሽ ከህመሙ ማገገም እንደጀመረ ቀድሞ ከሚወስደው በተጨማሪ አንዴ በየቀኑ ለሁለት ሳምንት ያህል መግቢው፡፡ ይህ በፍጥነት እንዲያገግም ይረዳዋል፡፡
 • ከህመማቸው የሚያገግሙ ሕፃናት ጥንካሬያቸው እና ክብደታቸው በቶሎ እንዲመለስ ከወትሮው በተጨማሪ ጡት ማጥባትና ተጨማሪ ምግብ በርከት አድርጎ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
 • በሕመሙ ምክንያት የምግብ ፍላጎታቸው ሙሉ በሙሉ ካልተመለሰ ተጨማሪውን ምግብ እንዲወስዱ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡

ለልጅ የሚያዘጋጅ ተጨማሪ ምግብ በጣትሽ እየቆነጠርሽ ልሰጪው የምትችይውን ያህል መወፈር አለበት፡፡ በኩባያና በማንኪያ መመገብ ትችያለሽ፡፡

 • ምግብነቱ ጥሩ የሆነ ገንፎ ወፈር ያለና በጣት ልትመግቢው የምትችይው መሆን አለበት አቅጥኖ መስጠት ልጅቷ በተገቢው መንገድ እንዳታድግ ያደርጋል፡፡
 • ወተት በኩባያ ወይም በጡጦ ማጠጣት ትችያለሽ፡፡ ከጡጦ ይልቅ የኩባያን ንጽሕና በቀላሉ መጠበቅ ስለሚሻል ኩባያ ተመራጭ ነው። ንፅህናው ያልተጠበቀ የወተት እቃ ልጅሽን በተቅማጥ በሽታ እንዲጠቃ ያደርጋል፡፡

ምግብ ከማዘጋጀትሽና ልጅሽን ከመመገብሽ በፊት እጅሽን በሳሙና መታጠብ ይኖርብሻል፡፡ ይህ የተቅማጥና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ያስወግዳል፡፡

 • ንጹህ ባልሆነ እጅ ምግብን መንካት የምግብ ብክለትን ሊያመጣ ይችላል፡፡
 • የመመገቢያ ዕቃዎች በሙሉ ንጹህ መሆን አለባቸው፡፡
 • ልጅሽን ግድ ካልሆነ በስተቀር በኩባያ ብቻ መግቢ፡፡ ለተቅማጥ በሽታ ስለሚዳርግ በፍጹም ጡጦ አይመከርም፡፡
 • ተቅማጥና ተላላፊ ህመሞችን ለመከላከል የልጁ ምግብ በጥንቃቄ ንጹህ ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡

ልጁ ፀሃይ ይሙቅ

ህፃናት 6 ወር ሲሞላቸው ፀሃይ መሞቅ ይኖርባቸዋል። የሕፃኑ ዕድገት የተስተካከለ እንዲሆን በየቀኑ ጥዋት ከ20 – 30 ደቂቃ ያህል ፀሐይ አሙቂው፡፡ የህፃናት ቆዳ ለፀሃይ ሲጋለጥ ቫይታሚን ዲ ማዘጋጀት ይጀምራል። ቫይታሚን ዲ ሰውነታቸው ካልሲየምን ተጠቅሞ ጠንካራ አጥንትና ጥርስ እንዲኖራቸው ያደርጋል። የቫይታሚን ዲ እጥረት ልምሻ የተባለውን በሽታን ያመጣል። ልምሻ ያለበት ህፃን
 • ደካማ አጥንት ይኖረዋል
 • ቶሎ መሄድ ያቅተዋል
 • የተጣመመ እግር፤ ያበጠ ወገብና ቁርጭምጭሚት ይኖረዋል
ስለዚህም ሰውነቱን በማይጎዳ መልኩ የጥዋት ወይም የማታ ፀሃይ ማሞቅ ይኖርብሻል። በምታሞቂው ሰአት ብርድ እንዳይመታውና ፀሃዩም ገላውን እንዳይጎዳው ተጠንቀቂ።

ልጅሽ ስድስት ወር እንደሞላው ቫይታሚን ኤ እንዲወስድ አድርጊ፡፡ ጠንካራ እንዲሆንም በየስድስት ወሩ ይውሰድ፡፡

 • ልጅሽ ከስድስት ወሩ አንስቶ አምስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በየስድስት ወሩ ወይም በዓመት ሁለት ጊዜ ቫይታሚን ኤ ማግኘት ስላለበት የጤና ባለሙያ እንዲሰጥሽ አድርጊ፡፡
 • ቫይታሚን ኤ ለልጅሽ ለእይታ ጠቃሚ ሲሆን በሽታንም መቋቋም እንዲችል ያደርጋል፡፡

ልጅሽ ሁለት ዓመት ሲሆናት በየስድስት ወሩ የአንጀት ትላትል ማጥፊያ የሚሆን መድሃኒት እንድትወስድ አድርጊ፡፡

 • ወደ ጤና ድርጅት በመሄድ ከ2 – 5 ዓመት ያለች ልጅሽን በዓመት ሁለት ጊዜ የአንጀት ትላትል ማጥፊያ መድሃኒት እንድትወስድ አማክሪ፡፡
 • የአንጀት ትላትሎች የደም ማነስ በማስከተል ልጅሽ ደካማና በሽተኛ እንድትሆን ያደርጋሉ፡፡

ቤተሰብ የሚመገበው ምግብ ሲያዘጅ አዮዲን የተጨመረበት ጨው መጠቀም ለቤተሰቡ ጤንነት ይረዳል፡፡

 • አዮዲን የተጨመረበት ጨውን በሁሉም ቦታ ለማግኘት ቢያዳግትም በተገኘ ጊዜ ሁሉ መጠቀም ይገባል፡፡
 • አዲስ የሚወለደው ሕፃን ጤንነቱ የተሟላ እንዲሆን እርጉዝ እናት አዮዲን ያለበትን ጨው መመገብ ይኖርባታል፡፡
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ