ከ 5 አመት በታች ያሉ ህፃናት እንክብካቤ

ጤናማና ደስተኛ ልጅ እንዲኖራቹ እንደቤተሰብ ሊኖራቹ የሚገቡ ባህርያትና ልታከናውኗቸው የሚገቡ ልምዶች በዝርዝር ከዚህ በታች ተጠቅመዋል። እነዚህ ባህርያትና ተግባራት ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንክብካቤን የተመለከቱ ሲሆኑ ልጆች እድሜያቸው ከፍ ያለም ቢሆን ግን ተጨማሪ እንክብካቤ መንፈግ የለብንም።

ሕፃኑ/ኗ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ በመስጠትና አነቃቂ አካባቢን በመፍጠር የሕፃኑ/ኗን አእምሯዊና ማኅበራዊ እድገት ያጎልብቱ።

 • ለሕፃናት አዎንታዊ ትኩረት መስጠትና በቂ ማበረታታት ማድረግ
 • ቋንቋ እንዲለምዱ ማነቃቃት
 • አዳዲስ የእንቅስቃሴ፣ የቋንቋና የማሰብ ክሂሎችን እንዲያገኙ መርዳት
 • ራሳቸውን ችለው አንድ ነገር የማድረግ የመሞከር ችሎታ እንዲያዳብሩ እድል መስጠት
 • እራሳቸውን ስለመጠበቅ መማር እንዲጀምሩ የሚያደርጉ እድሎች መስጠት
 • በማዋራት፣ በማንበብ፣ በመዝፈን የቋንቋ እድገታቸውን ማበረታታት
 • ከሌሎች ጋር መረዳዳትን፣ እና ለሌሎች ማካፈልን እንዲማሩ ማድረግ
 • የቅድመ ጽሑፍና የቅድመ ንባብ ክሂሎችን መሞከር
 • መማርን የሚያግዛቸውን – ራሳቸው እቃዎችን ማገላበጥ (መነካካት) – ተግባራት መፍቀድ
 • የጀመሩትን ሥራ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ራስን የመቆጣጠርና እስከመጨረሻው የመሥራት መንፈስን እንዲያዳብሩ ማበረታታት
 • ለሕፃኑ/ኗ መዝፈን፣ ታሪኮችን መንገር
 • ሕፃኑ/ኗን ማዳመጥና ቀላል መልሶች መስጠት
 • እንቅስቃሴን ከቃላት ጋር አቀናጅቶ በማውጣት ሕፃኑ/ኗ ደግመው እንዲሉት ማበረታታት
 • ማመስገንና ማቀፍን በመሳሰሉ መንገዶች ስሜትንና አድናቆትን መግለጽ ማስተማር

በሕፃናት ላይ የሚደርስ እንግልትና ኢሰብአዊ ድርጊት በወቅቱ ማወቅ፣ መከላከልና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ፡፡

በሕፃናት ላይ የሚደርስ እንግልትና ኢሰብአዊ ድርጊት ማለት በወላጆቻቸው፣ በአሳዳጊዎቻቸው፣ ወይም በሌሎች ተንከባካቢዎቻቸው የሚደረግ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ነው። የሕፃናት ጥቃት ዐይነቶች አካላዊ ጥቃት፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ መተው(ችላ መባል)፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ መጣል፣ እና ስድቦች ናቸው። በተንከባካቢ የሚፈጸም አካላዊ ጥቃት መበለዝን፣ መቃጠልን፣ በጭንቅላት ላይ ጉዳት ማድረስን፣ የአጥንት መሰበርን፣ እና የመሳሰሉትን ያካትታል። የአደጋዎቹ አስከፊነት ከቀላል ቁስለት እስከ ሞት የሚያደርሱ ናቸው። ወሲባዊ ጥቃት ባብዛኛው ከቤተሰብ ጋር የተገናኘ ሲሆን የሕፃኑ/ኗን ብልት መነካካት ወይም ሕፃኑ/ኗ የአዋቂውን ብልት እንድትነካካ መጠየቅን፣ አደጋ ሳያደርሱ የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸምንና አስገድዶ መድፈርን ያካትታል። ሕፃንን ችላ ማለት፣ ምግብ መስጠትን ችላ ማለት (ሆን ብሎ ምግብ መከልከል)፣ የህክምና እንክብካቤ እንዳያገኙ ችላ ማለትንና ጥበቃን ችላ በማለት ለአደጋ እንዲጋለጥ ማድረግ ሊሆን ይችላል። ህፃናት ሁሌም ከሚታመን አዋቂ ሰው/ተንከባካቢ ጋር መቆየት አለባቸው።

ወላጆችና ተንከባካቢዎች የሕፃናት ጥቃትን የሚጠቁሙትን የሚከተሉትን ምልክቶች በሚገባ መገንዘብ አለባቸው።
 • ሕፃኑ/ኗ ከሰዎች ጋር መነጋገርና መጫወት አለመፈለግ፣
 • ሕፃኑ/ኗ የተጨነቁ፣ ድንጉጥ፣እና የፈሩ ሲመስሉ ወይም አልጋቸው ላይ ሲሸኑ፣
 • በቆዳቸው ላይ መበለዝ ወይም ሠንበር ወይም ጠባሳ መታየት፣
 • በብልታቸው ወይም በፊንጢጣቸው ላይ ሽፍታ መኖር ወይም መቁሰል፣ ከሴቷ ብልት ደም መፍሰስ፣ ስትሸና ማቃጠል
 • ጥቃት ሲደርስ እንዳስፈላጊነቱ ልጅን ወደጤና ተቋም ወውሰድና ጉዳዩን ወደህግ ማቅረብ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው ሃላፊነት ነው።

ለታመሙ ሕፃናት ተገቢውን የቤት ውስጥ ሕክምና/እንክብካቤ መስጠት።

ሕፃኑ/ኗ እንደወትሯቸው መጫወት፣ መመገብ ወይም መጠጣት ሳይፈልጉ ከቀሩ ታመው ሊሆን ይችላል። ሕፃኑ/ኗ አንዳች የሕመም ምልክት ከታየባቸው በተቻለ ፍጥነት ወዲያውኑ የቤት ውስጥ ሕክምና/እርዳታ ማግኘት አለባቸው።
በቤት ውስጥ የትኩሳት ሕክምና
 • የሕፃኑ/ኗ የሰውነት ሙቀት በጣም ከፍተኛ ከሆነ አደገኛ ሲሆን ወደ መንቀጥቀጥ/መንዘፍዘፍ እና ራስን መሳት ሊያመራ ይችላል።
 • ሕፃኑ/ኗ ከፍተኛ ትኩሳት ካለባቸው የሰውነታቸውን ሙቀት ዝቅ ለማድረግ ልብሶቻቸውን ያውልቁላቸው፤ ውሃ በተነከረ ጨርቅ ሰውነታቸውን ያቀዝቅዙላቸው።
 • ሕፃኑ ተገቢውን ምርመራና ሕክምና እንዲያገኝ ወደጤና ማእከል መውሰድ።
በቤት ውስጥ የተቅማጥ ህክምና
ተቅማጥ ውሃንና ከምግብ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን ከህጻኑ/ኗ ሰውነት በማይፈለግ መልኩ ያስወጣል። በተገቢው መንገድ ካልታከመም የሰውነት መሟሸሽና ሞት ሊያስከትል ይችላል። ሕፃኑ/ኗ ተቅማጥ ከያዛቸው ሕይወት አድን ንጥረ ነገር (ORS) ወይም በቤት ውስጥ የተዘጋጀ ፈሳሽ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ማንኛውም ቤተሰብ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት እሽግ ሕይወት አድን ንጥረ ነገር በቤት ውስጥ ማስቀመጥና ተቅማጡ ወዲያው እንደጀመረ ሕይወት አድን ንጥረ ነገሩን መስጠት ይኖርበታል። ሕይወት አድን ንጥረ ነገር አዘገጃጀት
 • እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ
 • አንድ ሊትር የሚጠጣ ውሃ አፍልቶ ማቀዝቀዝ
 • አንድ እሽግ /ከረጢት/ የሕይወት አድን ንጥረ ነገርን (ORS) በአንድ ሊትር ተፈልቶ በቀዘቀዘ ውሃ መበጥበጥ
 • ሕይወት አድን ንጥረ ነገሩን በማንኪያ ወይም በኩባያ መስጠት
 • ሕይወት አድን ንጥረ ነገሩን በተከደነ እቃ ውስጥ ማስቀመጥ
 • የተበጠበጠው ሕይወት አድን ንጥረ ነገር በ24 ሰዓት ውስጥ ካላለቀ ተደፍቶ ሌላ መዘጋጀት አለበት
በቤት ውስጥ የሳል ህክምና
ሕፃኑ/ኗ ሳል በተያዙ ጊዜ ደጋግመው ጡት መጥባት ይኖርባቸዋል፤ ብዙ ፈሳሽና ምግብም መውሰድ አለባቸው። ብዙ ፈሳሽ መውሰድ የሳሉን ተደጋጋሚነትና ኃይለኝነት በመቀነስ የጉሮሮን ሕመም ይቀንሳል። በጤና ሠራተኛ ካልታዘዘ በስተቀር ለሕፃናት የሳል መድኃኒቶችን መስጠት ተገቢ አደለም።

በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መከላከልና ጉዳት ሲደርስባቸው ተገቢውን ሕክምና መስጠት

ሕፃናት ብዙ ጊዜ ለተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭ ናቸው። ስለዚህም ወላጆች/ተንከባካቢዎች የተለመዱትን ጉዳቶች ለመከላከልና ለማከም በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ማግኘታቸው ጠቃሚ ነው። በሕፃናት ላይ የሚያጋጥሙ የተለመዱ የጉዳት ዓይነቶች፡- በእሳትና በትኩስ ነገር መቃጠል፣ መውደቅ፣ ባዕድ ነገሮች ወደ መተንፈሻ አካላትና ወደ ጆሮ መግባት፣ መመረዝ፣ በእንስሳት መነከስ፣ በነፍሳት መነደፍና መታፈን ናቸው። አደጋዎችን መከላከያና ጉዳቶችን መቆጣጠሪያ መንገዶች፦
 • ስለት ያላቸውን ነገሮች ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ በማስቀመጥ ከመኖሪያ አካባቢዎች በማስወገድና በአግባቡ በሰውነት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መከላከል፣
 • ሁሉንም መድኃኒቶች፣ ነጭ ጋዝና ሌሎች አደጋ የሚያስከትሉ ኬሚካሎችን ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ በማስቀመጥ መመረዝን መከላከል፣
 • በሁሉም የመድሃኒት ማስቀመጫ እቃዎች ላይ በግልጽ እንዲታይ አድርጎ ስማቸውን መጻፍ፣
 • እሳት ካለበት ቦታ በማራቅ፣ ከፍ ያለ ማንደጃ ቦታ በመጠቀም፣ ኩራዞችንና ክብሪቶችን ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ በማስቀመጥ ሕፃናትን ከመቃጠል መጠበቅ፣
 • የአየር መተላለፊያን ሊዘጉ የሚችሉ ነገሮችን ለምሳሌ ላስቲኮችን/ፌስታሎችን፣ ጨቅላ ሕፃናትን ሊያፍኑ የሚችሉ ትራሶችን፣ ጥራጥሬዎችን፣ የብርእ እህሎችን የመሳሰሉትን ከሕፃናት በማራቅ፣
 • ትንታን ለመከላከል የሚጫወቱበትን እቃዎች (አሻንጉሊቶችን) ጥቃቅን ክፍሎች፣ ጥራጥሬዎችና የብርእ እህሎች ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ
በአጠቃላይ ሕፃናትን ስለት ካላቸው ነገሮች፣ ከፈላ ውሃ፣ ከእሳት፣ ከከፍተኛ ቦታ (እንዳይወድቁ) እና ከሚያንቁ ነገሮች ማራቅ፣

ጎጂ ባህላዊ ልማዶችን ማስወገድ (እንጥል ማስቆረጥ፣ ጉሮሮ ማስቧጠጥ፣ የሴት ልጅ ግርዛት ወዘተ)።

ጎጂ ልማዶች የሚባሉት በአንዳንድ ምክንያቶች እውቀቱ/ሙያው በሌላቸው ሰዎች በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙና አካላዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ተግባራት ናቸው። እነዚህ ተግባራት ብዙ ጊዜ በሕፃናቱ ላይ የአጭር ወይም የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስከትላሉ። በጣም የተለመዱት ጎጂ ልማዶች እንጥል ማስቆረጥ፣ ጉሮሮ ማስቧጠጥ፣ ግግ ማስወጣት፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ እና የቅንድብ መሸንሸን (መብጣት) ናቸው።

ብዙዎቹ ጎጂ ድርጊቶች የሚከናወኑት ለተለያዩ የበሽታ ዐይነቶች ሕክምና ናቸው በሚል ምክንያት ነው። እንጥል ማስቆረጥ ጨቅላ ሕፃናት ጡት መሳብ ሲያቅታቸውና ሲያስታውካቸው፤ጉሮሮ ማስቧጠጥ ሕፃናት ጉሮሯቸውን ሲያማቸውና የቶንሲል እጢዎች ሲያብጡባቸው፤ ግግ ማስወጣት ሕፃናት ተቅማጥ ሲይዛቸው፤ የቅንድብ መሸንሸን ደግሞ ሕፃናት በዐይን በሽታ ሲታመሙ የሚደረግ ነው። ሁሉም ተግባራት የሕፃናቱን የተለመደውን በሽታ የመከላከል ሂደት በመረበሽ/በማቋረጥ ተሕዋስያን ወደሰውነታቸው እንዲገቡና ለከፋ በሽታ ያጋልጧቸዋል። ስለዚህም እንደ መንጋጋ ቆልፍና ኤችአይቪ/ኤድስ ባሉ በሽታዎች በቀላሉ ሊያዙ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም የደም መፍሰስ ከነዚህ ተግባራት ጋር የሚመጣ ተያያዥ ችግር ነው። በሽታን በተገቢው መንገድ በቤት ውስጥ በማከምና በአፋጣኝ ከሰለጠኑ ባለሙያዎች የጤና እንክብካቤን በመሻት እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮችን መከላከል ይቻላል።

ሙሉ ክትባትን ለመጨረስ ሕፃናትን በቀጠሮ ቀኖቹ ወደ ህክምና ተቋም ይውሰዱ።

ክትባት ህፃናት ላይ ሞትንና ጉዳትን ከሚያመጡ በሽቶች ስለሚከላከል ክትባታቸውን በጊዜ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ስለክትባት የተፃፈውን ሙሉመረጃ ያንቡ።

የታመሙ ሕፃናት ተጨማሪ ህክምና በሚያስፈልጋቸው ወቅት ፈጥኖ መርዳትና ተገቢውን ህክምና ከሰለጠነ ባለሙያ እንዲያገኙ ማድረግ።

ብዙ ሕፃናት የሚሞቱት የሕፃኑ/ኗ ሁኔታ ክፉኛ ተባብሶ የቤት ውስጥ ህክምናውን መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተንከባካቢዎቹ በወቅቱ ማወቅ ባለመቻላቸው ምክንያት ነው። ስለዚህም እንክብካቤ ሰጭዎች የአደጋ ምልክቶችን መገንዘብ አለባቸው፡፡ በታመመ/ች ሕጻን ላይ የሚታዩ አደገኛ ምልክቶች ቶሎ መለየትና የጤና እንክብካቤን የሕጻኑን ቶሎ መሻት ቶሎ የመዳንንና የመኖር እድል ያሳድጋል፡፡

የታመመ ሕፃንን ሁኔታው እየባሰ መምጣቱን የሚያሳዩ አደገኛ ምልክቶች፡-
 • ሕጻኑ መጠጣትና መብላት ሲያቆም ወይም ሲያቅተው፣
 • የበላውን ሁሉ የሚያስታውክ ከሆነ፣
 • መንዘፍዘፍ ወይም ራስን መሳት፣
 • ሕፃኑ እንቅልፍ እንቅልፍ ካለው ወይም ራሱን ከሳተ ማለትም ለማንኛውም የማነቃቃት ጥረት በደንብ መልስ የማይሰጥ ከሆነ፣
 • ደም ያለው ተቅማጥ፣
 • የአንገት ወይም ማጅራት መገተር፣
 • ትኩሳት፣ (ከሁለት ቀን በላይ ሲቆይ)
የሕፃናት ሕይወት በጣም በቀላሉ ለአደጋ የሚጋለጥ በመሆኑ ከሰለጠኑ የጤና ሠራተኞች የጤና እንክብካቤ መሻት የግድ ያስፈልጋል። ሕፃናት ብዙ ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ በሽታዎች በአንድ ጊዜ ይታዩባቸዋል፤ ስለዚህ የጤና እንክብካቤ ለመሻት ምንም ዐይነት መዘግየት ከኖረ ከባድ ተዛማጅ የጤና ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።

ሕክምና ክትትልና ወደከፍተኛ ጤና ተቋም መሄድን በተመለከተ በጤና ባለሙያ የሚሰጥን ምክር ማክበር።

ት ሲታመሙና ወደጤና ሠራተኛ ሲወሰዱ ሕክምና የሚደረግላቸው በሕመማቸው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ በመመስረት ነው። ሕመማቸው በጣም ከባድ ካልሆነ በተንከባካቢዎቻቸው ድጋፍ በቤታቸው ውስጥ የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ይሰጧቸዋል። ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ሞት ዋና ዋና ምክንያቶች ለሆኑት በሽታዎች ሕክምና የሚሆኑ መድኃኒቶችን (ለሳንባ ምች ፀረ ተህዋሲያን (Antibiotic)፣ ለተቅማጥ የሕይወት አድን ንጥረ ነገር /ORS/፣ ለወባ የፀረ ወባ መድኃኒት) በጤና ኬላ ደረጃ ማግኘት ይቻላል። መድኃኒቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ሕፃናት በየቀኑ እንዲወሰድ የሚታዘዘውን መጠን ያህል እና ለታዘዘው ጊዜያት መወሰድ አለባቸው። መድኃኒቶች በጤና ሠራተኞች በታዘዘው መሰረት ካልተሰጡና ያለአግባብ ከተወሰዱና በየመሀሉ ከተቋረጡ ወይም ሙሉ በሙሉ ካልተሰጡ አይሠሩም። በዚህም ምክንያት የታመመው/ችው ሕፃን መሻሻል አያሳዩም፤ በሽታውም ይባባሳል። ስለዚህም ተንከባካቢዎች የጤና ሠራተኞች ያዘዙትን የመድኃኒት አወሳሰድ የግድ መከተል አለባቸው።
 • ሕፃናት ከህመማቸው የሚፈወሱት የታዘዘላቸውን ህክምና ሲያጠናቅቁ ነው፡፡
 • ልጅዎ ከህመሙ ቢያገግምም በቀጠሮ ቀን ለክትትል ወደ ጤና ሠራተኞች ይውሰዱ፡፡
 • ሕፃናት ወደ ሌላ ሕክምና ድርጅት የሚተላለፉት ለበለጠ ሕክምናና እንክብካቤ ስለሆነ፣ ሕፃኑን ወደ ሚቀጥለው የጤና ተቋም ለመውሰድ ማንኛውንም ጥረት ያድርጉ፡፡
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ