እርግዝናን መከላከል

ባልና ሚስት የሚወልዱበትን ጊዜ ከ3-5 ዓመት ካራራቁ የሕፃኑ/ኗም የእናትየዋም በሕይወት የመቆየት እድላቸው ይጨምራል። ይህም ባልና ሚስት እርግዝና ከመሞከራቸው በፊት የመጨረሻው ልጅ ከተወለደ በኋላ 2 ዓመት መጠበቅ አለባቸው ማለት ነው። ከወሊድ በኋላ ባሉት 2 ዓመታት ውስጥ እርግዝና ከተከሰተ ለጤና ችግር የመጋለጥ እድሉ ይጨምራል። የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴ መቼ መጀመር እንዳለብሽ የሚወሰነው በጡት ማጥባት ሁኔታሽ፣ በምትመርጪው ዘዴና በተዋልዶ ጤና ግባቹ ነው።
በመጨረሻው የቅድመ ወሊድ ቀጠሮ (ከወለድሽ ከ 6ሳምንት በኋላ)መጠቀም የምትፈልጊውን የእርግዝና መከላከያ መንገድ እንድትመርጪ ውጤታማ የሆነ የቤተሰብ ዕቅድ የምክር አገልግሎት ይሰጥሻል። ውጤታማ የሆነ የቤተሰብ ዕቅድ የምክር አገልግሎት እርግዝና መከላከያ ለመጠቀም መፈለግን ስለሚጨምር፣ ውጤታማ አጠቃቀምን ስለሚያበረታታ፣ ሳያቋርጡ መጠቀምን ስለሚያሻሽል፣ የተገልጋይ እርካታን ስለሚያስገኝ፣ አሉባልታና የተሳሳተ አመለካከትን ስለሚያስወግድ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። የሚከተሉት የቤተሰብ ዕቅድ ዘዴዎች በድኅረ ወሊድ ወቅት ሊቀርቡ የሚችሉ አማራጮች ናቸው።

ጡት በማጥባት እርግዝናን የመከላከል ዘዴ

በእንግሊዝኛው Lactational Amenorrhea Method (LAM) የተባለው ዘዴ መጠሪያውን ያስገኙለት ቃላት ፍቺ የሚከተለው ነው። Lactational ማለት ከጡት ማጥባት ጋር የተገናኘ፣ Amenorrhea ማለት የወር አበባ አለማየት ሲሆን Method ደግሞ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ማለት ነው። ስለዚህ Lactational Amenorrhea Method (LAM) በማጥባት የወር አበባን የሚያስቀር የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ማለት ነው። በማጥባት እርግዝናን የመከላከል ዘዴ (LAM) በሦስት መስፈርቶች የሚበየን ነው፡-
 • የወር አበባሽ መምጣት ካልጀመር፣
 • ልጅሽ ሙሉ በሙሉ ጡት ብቻ በመጥባት የሚመገብ/የምትመገብ መሆኑ፣ እና
 • የልጅሽ ዕድሜ ከ6 ወር በታች መሆኑ

ለምታጠባ ሴት ሌሎች አማራጮች

በማጥባት እርግዝናን የመከላከል ዘዴ ባትጠቀሚም እስከ ስድስት ሳምንት ድረስ እርግዝና አይኖርም። በ6ኛው ሳምንት ፕሮጅስቲን ብቻ የተባለ ንጥረ ነገር የያዙ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን ያለችግር መጠቀም ትችያለሽ። እነዚህ እንክብሎች ካልተገኙ በመርፌ የሚሰጡ (ለምሳሌ “Depo Provera” ወይም በክንድ ላይ የሚቀበር “implant” መጠቀም ትችያለሽ፡፡ ጥንድ ሆርሞኖችን የያዙ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች የጡት ወተትን መጠን እንዲሁም ጥራት ስለሚቀንሱ የሚያጠቡ እናቶች እንዲጠቀሙ አይመከርም፡፡
 • ከወሊድ በኋላ ባለው 48 ሰዓት ውስጥ፣ በ4ኛው ሳምንት ወይም ከዚያ በኋላ ባለው የድኅረ ወሊድ ወቅት በማኅፀን ውስጥ የሚቀመጥ የእርግዝና መከላከያ (ሉፕ) መጠቀም ትችያለሽ፡፡
 • ኮንዶም በማናቸውም ጊዜ መጠቀም ይቻላል
 • መውለድ ሙሉ በሙሉ ማቆም ለሚፈልጉ የማኅፀን ቱቦ ማሳሰር ወይም የወንድ ዘር መተላለፊያ ቧንቧውን ማስቆረጥም ይቻላል፡፡

ለማታጠባ ሴት

ጡት አለማጠባት የማይመከር ተለምዶ ቢሆንም ጡት የማታጠባ ሴት የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ከመጀመሪያው የግብረስጋ ግንኙነት በፊት መጀመር አለባት።
 • ፕሮጅስቲን ብቻ የተባለ ንጥረ ነገር የያዙ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን ከወሊድ በኋላ ወዲያው መጀመር ይቻላል፣
 • ከወሊድ በኋላ ከ3 ሳምንታት ጀምሮ ጥንድ ሆርሞኖችን የያዘውን የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን መጠቀም ይቻላል፣
 • ከወሊድ በኋላ ባለው 48 ሰዓት ውስጥ፣ በ4ኛው ሳምንት ወይም ከዚያ በኋላ ባለው የድኅረ ወሊድ ወቅት በማኅፀን ውስጥ የሚቀመጥ የእርግዝና መከላከያ (ሉፕ) መጠቀም ትችያለሽ፡፡
 • ኮንዶም በማናቸውም ጊዜ መጠቀም ይቻላል
 • መውለድ ሙሉ በሙሉ ማቆም ለሚፈልጉ የማኅፀን ቱቦ ማሳሰር ወይም የወንድ ዘር መተላለፊያ ቧንቧውን ማስቆረጥም ይቻላል፡፡
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ