ስለእናት

ይህ ወር እንደገባ የእርግዝና ምልክቶችን ማስተዋል ትጀምርያለሽ። የወር አበባሽ ሲቀርም በምርመራ ማረጋገጥሽ አይቀርም። ታድያ እርጉዝ መሆንሽን እንዳወቅሽ የቅድመ ወሊድ ክትትል መጀመር ይኖርብሻል። በተጨማሪም ስለምትበያቸው ምግቦች፤ ስለምትጠጫቸው መጠጦች፤ ስለምትወስጅው መዳኒትና ስለምታደርጊው እንቅስቃሴ ማሰብ ይኖርብሻል። እርግዝና በሚል እርእስ ውስጥ ያስቀመጥነውን መረጃ በደንብ ማንበብና እስክትወልጂ ድረስ መተግበር ይኖርብሻል። ስለ ቅድመ ወሊድ ክትትል ያሰፈርነው መረጃም በያንዳንዱ የህክምና ቀጠሮ ላይ ዝግጁ እንድትሆኚ ስለሚረዳ ብታነቢው ይመከራል።
እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ መጠነኛ የደም መፍሰስ ሊኖር ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ችግር የሚያመጣ ባይሆንም የውርጃ ወይም የእንግዴ ልጅ ችግርን ሊያመላክት ስለሚችል ምንም አይነት ደም መፍሰስ ካለ ሃኪም ማማከር ይኖርብሻል። በእርግዝና ሰአት ሊታዩ የሚችሉ አደገኛ ምልክቶችን ማወቅ ባፋጣኝ የጤና እርዳታ እንድታገኚና ጉዳት ሳይደርስ ችግሩ መፍትሄ እንዲሰጠው ስለሚረዳ አደገኛ ምልክቶችን እንደራስሽ ስም ማወቅ ይጠበቅብሻል።
የመጀመርያው ሶስት ወር አስቸጋሪው ወር ሊሆንብሽ ይችላል። ይህም ከእርግዝና ጋር ተያይዘው በሚመጡ ምልክቶች የተነሳ ነው። በተለይ ማቅለሽለሽ ሲበዛም ማስታወክ ምግብ እንዳትበይ በማድረግ ሊያዳክምሽ ይችላል። የፅንሱ ፈጣን እድገትም በራሱ ድካምንና ቶሎ ቶሎ መሽናትን ያስከትላል። ስለእርግዝና ምልክቶችና ማቅለያ መንገዶች ያስቀመጥነውን በማንበብ ቀለል እንዲልሽ አድርጊ።

ስለፅንሱ

በዚህ ወር መጨረሻ ልጅሽ የሚያስፈልጋት የሰውነት አካል በሙሉ ማደግ ይጀምራል። አይምሮ፣ እጅና እግር፣ አይንና አፍንጫ፣ ሳንባና ልብ፣ ኩላሊትና ጉበት … ሁሉም የሰውነት ክፍል ሲኖራት ሁሉም ግን በበቂ ሁኔታ ለማደግ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በተለይ አይምሮና ሳምባ እስከሚወለዱበት ቀን ድረስ እድገታቸው የሚቀጥል ይሆናል።
አሁን ባላት አቋም ጭንቅላቷ ትልቁን ቦታ ሲወስድ ከጭንቅላቷ በታች ያሉት የሰውነት ክፍሎች በመጠን ያንሳሉ። ይህ እያደገች ስትመጣ የሚስተካከል ይሆናል። አይኗ አፍንጫዋና ጆሮዋ ወጣ ብለው ባይታዩም ቦታው ላይ የማደግ ምልክት ማሳየት ይጀምራሉ። እጅና እግሯም ጣቶች ቢኖሯቸውም የተያያዙ በመሆናቸው በደንብ ተለይተው አይታዩም። ግር ሊያሰኝ የሚችልም ጭራ መሳይ አካል ይኖራታል። ይህም እያደገች ስትሄድ የሚጠፋ ነው።
ከሁሉም አስቀድሞ ስራ የሚጀምረው ልቧ ሲሆን በዚህ ሰአት በደቂቃ ከ 100 እስከ 160 ጊዜ ድረስ ይመታል – ያንቺን የልብ ምት እጥፍ እንደማለት ነው። ይህን የልብ ምት ድምፅ በሚቀጥለው ወር በሚኖርሽ የአልትራ ሳውንድ ምርመራ ጊዜ የምትሰሚው ይሆናል። ልጅሽ በአፋጣኝ የምታድግበት ጊዜ በመሆኑ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይኖርብሻል። በወሩ መጨረሻ በአይን ብትታይ ቦሎቄ ታክላለች
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ