ስለእናት

የወገብና የእግር ህመሙ እየከበደ እንደሚሄድ አምነሽ ተቀብለሻል ብለን እናስባለን። እነዚህ ህመሞች ሲበረቱ እረፍት እንደሚያስፈልግሽ ግን ተገንዘቢ። የልጅሽ እንቅስቃሴ ጠንካራ ከሆነና በመተኛ ሰአትሽ እንቅስቃሌ ካበዛ እንቅልፍ ማጣትሽ የማይቀር ነው። ነገር ግን ከወለድሽ በኋላ ለማጥባት ለሊት በተደጋጋሚ መነሳትሽ ስለማይቀር ካሁኑ መለማመድም ጥሩ ነው።
የደም ዝውውርሽ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የልብ ምትሽ ሊፈጥን፤ ትንፋሽ ሊያጥርሽና ሊያዞርሽ ይችላል። የሚያስጨንቅ ነገር ባይሆንም እራስሽን መጠበቅና እረፍት ማረግ እንዳለብሽ ማመላከቻ ነው። ክብደትሽ እየጨመረ በመሆኑ እግርሽ መጨመሩ አይቀርምና በልክሽ ጫማ መግዛት ይኖርብሽ ይሆናል። ቃርና የሆድ ድርቀት እንደገና ሊጀምርሽ ይችላል ማቅለያ መንገዶቹን ተከተይ።
አደገኛ የሚባሉትን የእርግዝና ምልክቶች በደንብ መከታተል ይኖርብሻል። የልጅሽን እንቅስቃሴ አጥኚ እንቅስቃሴው ሲዳከም ቶሎ እንድታቂ ይረዳሻል። አብዛኞቹ በእርግዝና ሰአት የሚከሰቱ ውስብስብ ችግሮች እርግዝና በገፋ ቁጥር የመከሰት እድላቸው ሰፊ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ለሁሉም ነገር መፍትሄው የቅድመ ወሊድ ክትትልሽን በተገቢው መንገድ መከታተል ነው። በዚህ ወር በሚኖርሽ የቅድመ ወሊድ ቀጠሮ አር ኤች ኔጌቲቭ ከሆንሽ የልጅሽን ደም የሚያጠቃ ህዋስ ልታመርቺ ስለምትችይ እሱን የሚከላከል መዳኒት ትወጊያለሽ። ይህም ሾተላይ ተብሎ የሚታወቀውን ችግር ይከላከላል።

ስለፅንሱ

የአይምሮው እድገት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በአካል ብቻ ሳይሆን በተግባርም እንደአራስ ልጅ መሆን ይጀምራል። ይህን ወር ልጅሽ በተመሳሳይ ሰአት መተኛትና መነሳት ይጀምራል። አንቺ ስትተኚ እንዲተኛ ፀልይ። እያደገ ሲመጣ የእንሽርት ውሃው እየቀነሰ ቦታውን ለፅንሱ ይለቃል። አይኑን መግለጥና መክደን እንዲሁም እጁን መምጠት የቀን ለቀን ትግባሩ ነው። አይኑን መግለጥም ሆነ ብርሃን መለየት ቢችልም በአብዛኛው ጊዜ ግን የተከደነ ይሆናል። ይህ ከተወለደም በኋላ የሚቀጥል ሲሆን አራስ ሆኖም በሚገልጥ ሰአት በጣም ቅርብ ከሆኑ ነገሮች ውጪ ማየት አይችልም።
ሳንባው ሙሉ መሙሉ ባያድግም በዚህ ወር ቢወለድ በህክምና እርዳታ የመኖር እድል አለው። ከዚህ ወር ጀምሮ ስቅታ ስለሚጀምር ሊሰማሽ ይችላል። የተወሰኑ ደቂቃዎችን ብቻ የሚቆይ ሲሆን ላንቺም ለልጁም ጉዳት አያመጣም። ስቅታ በተለምዶ የልጆችን ደረት ያሰፋል በመባል እንደጥሩ ነገር የሚወሰድም ነው።
ሰውነቱ እና አይምሮ በፍጥነት እያደገና በደንብ እየጨመረ ስለሆነ ፕሮቲን፣ ቫይታሚን ሲ፣ ፎሊክ አሲድና አይረን ያላቸው ምግቦችን ተመገቢ። ለአጥንቱ ጥንካሬም ደግሞ ወተት ወይም የወተት ተዋፅኦ የሆኑ እንደ እርጎና አይብ ያሉ ምግቦችን ተመገቢ። ልጅሽ በየቀኑ እስከ 250 ሚሊ ግራም ካልሲየም ለአጥንቱ ጥንካሬ ይጠቀማል።

በወሩ መጨረሻ
  • ከ 1 እስከ 1.35 ኪሎ ግራም ይመዝናል
  • 40 ሴንቲ ሜተር ይረዝማል
  • በአይን ቢታይ ትልቅ ጥቅል ጎመን ያክላል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ