ስለእናት

እንኳን ደስ አለሽ የመጨረሻው ወር ላይ ደርሰሻል። ሆዴ መቼም ከዚህ በላይ የትም ሊሄድ አይችልም እያልሽ ነው አደል? እመኚን በዚህ ወር መጀመርያ በደንብ ይጨምራል። ከ 37 ሳምንት በኋላ ግን መጨመር ያቆማል – ተፈጥሮ ነገሮችን የምታሳካበት መንገድ አላት። ይህ የመጨረሻ ወር ስለሆነ የቅድመ ወሊድ ቀጠሮሽ በየሳምንቱ ይሆናል። እነዚህ ቀጠሮዎች በወሊድ ጊዜ ያልታሰበ ነገር እንዳይፈጠር አስቀድሞ ጥንቃቄ በማድረግ ጤነኛ የወሊድ ጊዜ ከጤነኛ ልጅ ጋር እንዲወለድ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
መውለጃ ቀንሽ መቅረቡን አስመልክቶ ሆድሽ (ልጅሽ) ወደታች ይወርዳል። ይህም የአተነፋፈስና የቃር ችግሮችን ቀለል እንዲል ሲያደርግ ነገር ግን መራመድ እንዲከብድሽ ያደርጋል። በተጨማሪም ፊኛሽ ላይ የሚፈጥረው ጫና ሽንትሽን ቶሎ ቶሎ ሊያመጣውና ወደ መፀዳጃ ቤት ሊያመላልስሽ ይችላል። የእግር ማበጥም በዚህ ወር የተለመደ ሲሆን እብጠቱ ግን ድንገተኛ ከሆነና በተለያዩ የሰውነት ክፍሎችሽ ላይ ከታየ የፕሪ ኢክላምዚአ ምልክት ሊሆን ስለሚችል ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይኖርብሻል። እራስሽ ላይ የምታያቸው ለውጦት የአደገኛ ምልክቶች አለመሆናቸውን ለማወቅ ሁሌም በእርግዝና ሰአት ሊታዩ የሚችሉ አደገኛ ምልክቶች ምን ምን እንደሆኑ ማወቅና ማንበብ ይኖርብሻል።
  • ይህ ጊዜ የምጥ ምልክቶችን ጠንቅቀሽ ማወቅ የሚጠበቅብሽ ወቅት ነው። በተለይ የእንሽርት ውሃ መፍሰስና ከጀርባ ጀምሮ ወደፊት የሚመጣን ቁርጠትን በደንብ መከታተል ይኖርብሻል። በነገራችን ላይ ይወለዳል በተባለው ቀን ይወለዳል ብለሽ አታስቢ ወደፊት ሊመጣ ወይም ወደኋላ ሊቀር ይችላል – ልጅሽ ቀኑ ስለደረሰ ሳይኖን ዝግጁ ሲሆን ነው የሚወለደው።
ወሩ እያለቀ ሲሄድ ለወሊድ የሚያስፈልጉሽን ነገሮች አዘጋጂ፤ ወደ ሃኪም ቤት ስትሄጂ የምትይዣቸውን ነገሮች በቦርሳ አርገሽ ቅርብ ቦታ አስቀምጪ። መዘገጃጀት እንዳለ ሆኖ እራስሽን ግን አታድክሚ ለምጥ ሃይል ያስፈልግሻልና ሀይልሽን ቆጥቢ። ስለምጥና ወሊድ አስፈላጊ መረጃዎችን ማወቅ በጣም ጠቃሚ በመሆኑ በወሊድ ስር የተቀመጡ ፅሁፎችን እንድታነቢ እንመክራለን። በተረፈ ግን ትንፋሽ ውሰጂ፤ ተረጋጊ፤ ልጅሽን ለማየትና ለማቀፍ ተዘጋጂ። ከወሊድ በኋላም አብረንሽ ነን!!

ስለፅንሱ

መወለጃው ሲደርስ ገላውን ሸፍኖት የነበረው ጸጉርና ቆዳውን ከእንሽርት ውሃ ሲከላከለው የነበረው ዘለግላጋና ነጭ ሽፋን መርገፍ ይጀምራሉ። እነዚህንም መልሶ በመዋጥ እንደተወለደ የሚኖረውን ጥቁርና ዘለግላጋ ሰገራ ያጣራል። ለወሊድ ዝግጁ በመሆንም ጭንቅላቱ ወደታች ያዞራል። በዚህ ወር መጨረሻ ልጅሽ ለመወለድ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ይሆናል። ሆኖም ከተወለደ በኋላ ለተወሰኑ ሳምንቶች ቆዳው ይላላጣል፤ በደምብ ማየት አይችልም፤ ሰውነቱ እጥፍጥፍ ያለ ይሆናል – የውጭውን አለም ለመልመድ ጊዜ ያስፈልገዋል።
በወሩ መጨረሻ አጥንቱ በጣም ጠንካራ በመሆኑ እንደተወለደ ጣትሽን ብትሰጪው አጠንክሮ ይይዛል። ሰውነቱ ሙሉ ለሙሉ በማደግ ውጪ ለሚጠብቀው ህይወት ዝግጁ ይሆናል። ጭንቅላቱም ጸጉር በማብቀል ሲወለድ ሰው እንዲመስል ይረዳዋል። ከ 37 ሳምንት በኋላ መውለድ ፅንሱ ላይ ችግር ባያመጣም ማህፀን ውስጥ በቆየ ቁጥር አይምሮውና ሳንባው በተሻለ መንገድ ያድጋል። የጤና ችግር ቢኖርና በቀዶ ጥገና መውለድ ቢኖርብሽም እንኳን አስገዳጅ ጉዳይ ከሌለ በስተቀር እስከ 40 ሳምንት ትጠበቂያለሽ። ታዲያ በነዚ ጊዜያቶች ከአይምሮና ከሳንባ እድገት በተጨማሪ ሰውነቱን በቅባት ይሸፍናል። ይህ ቅባትም ሰውነቱን ከብርድ የሚከላከልበት መንገድ ነው። ሆኖም ምንም ብርድ ሳይነካው ማህፀን ውስጥ 9 ወር የኖረ ህፃን ሲወለድ ሙቀቱን መቆጣጠር ሊያቅተው ይችላል። ለዛም ነው እንደተወለደ ከናትየው ሰውነት ጋር ንክኪ እንዲኖረውና ሙቀት እንዲያገኝ የሚደረገው።
ምንም እንኳን ጤነኛ እርግዝና ብታሳልፊም ሁሌም በጤና ማእከል መውለድ የተሻለ መሆኑን አምነሽ በጤና ተቋም ውለጂ። በጤና ተቋም መውለድ ልጅሽ የሚያስፈልገውን የመጀመርያ ቀን ክትባትም እንዲያገኝ ያግዘዋል። አንድ ህፃን በተወለደ እለት የሳምባ ነቀርሳና የልጅነት ልምሻን የሚከላከል ክትባት ያገኛል። ይህም ለጤናማ እድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በወሩ መጨረሻ
  • ከ 3 እስከ 3.5 ግራም ይመዝናል
  • 50-55 ሴንቲ ሜትር ይረዝማል
  • በአይን ቢታይ ትልቅዬ ዱባ ያክላል … አሁንማ እራስሽ በአይንሽ ታይዋለሽ።
  • በድጋሚ እንኳን አይንሽን በአይን ለማየት አበቃሽ።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ