ስለእናት

ሆድሽ በጣም በመግፋቱ ከዚህ በፊት የምታደርጊያቸውን ነገሮች በሙሉ ማረግ ይከብድሽ ይሆናል። እኛ የምንመክርሽ በተቻለሽ አቅም እረፍት ውሰጂ። ይህን ጊዜ መልሰሽ አታገኚውም ልጅሽ ከመጣች በኋላ እረፍት ምን ማለት እንደሆነ ሊጠፋሽ ይችላል። የልጅሽ እድገት ሲጨምርና ሆድች ወደላይ ከፍ ሲል የደረት አጥንትሽ ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል – ህመምም ሊኖረው ይችላል። ከጡትሽ ላይም ቢጫ መልክ ያለው ፈሳሽ ሊወጣ ይችላል – ሊያስደነግጥሽ አይገባም። አንዳንድ ነብሰጡሮች ከመውለዳቸው በፊት ጡታቸው ወተት ማፍሰስ ይጀምራል። ይህም ቢጫ ወተት አንገር ይባላል።
ከስምንት ወር ጀምሮ የውሸት ምጥ የሚባለው ምልክት መታየት ይጀምራል። የውሸት ምጥ ወይም በተለምዶ መንገድ ጠራጊው የሚባለው እውነተኛ ምጥ ያልሆነና ወደ ወሊድ የማያመራ ነው። የእውነተኛና የውሸተኛ ምጥን ልዩነት ማወቂያ ጊዜሽ አሁን ነው። ሙሉ መረጃውን ወሊድ በሚለው ማውጫ ስር ምጥ የሚለውን ዝርዝር ፅሁፍ ተመልከቺ።
በሌላ በኩል ወሊድ መቅረቡን አስመልክቶ ሆርሞኖችሽ መገጣጠሚያሽ እንዲላላ በማረግ ክብደትሽን የመሸከም አቅም ያሳጡሻል። ይህም ወገብሽ ላይና እግርሽ ላይ ጫና በማድረግ ህመም ሊያመጣ ይችላል። መፍትሄው? እረፍት። ይህ መውለጃሽ እየቀረበ መሆኑን ስለሚያመላክት የምትወልጅበትን ቦታ (ሀኪም ቤት እንዲሆን አበክረን እንመክራለን)፤ የሚያስፈልግሽን ገንዘብ፤ የሚያርስሽንና የሚያግዝሽን ሰው ማዘጋጀት ይኖርብሻል። ዘጠኝ ወር ሲገባ ሊከብድሽና ድካም ድካም ሊልሽ ስለሚችል ለወሊድ የሚያስፈልጉሽን ነገሮች በዚህ ወር ብታሟዪ ላንቺ ጥሩ ነው። ስለወሊድ ያስቀመጠነውን መረጃ በሙሉ ብታነቢ በጣም ጥሩ ነው።

ስለፅንሱ

በስምንተኛው ወር መጨረሻ ከሳምባዋ በስተቀር ሌሎቹ የሰውነት ክፍሎቿ በደንብ አድገው ይጨርሳሉ። በዚህም የተነሳ የተቀሩትን ጊዜያቶች ክብደት በመጨመር ትጠመዳለች። አንቺ ከምትጨምሪው እያንዳንዱ ኪሎ ግማሹ የሷ ክብደት ነው። ስትወለድ ከሚኖራት ክብደት ከግማሽ በላዩን ከዚህ ወር ጀምሮ የምትጨምረው ይሆናል። በፊት ከነበራት እንቅስቃሴ ግን በጣም ትቀንሳለች – መጥፎ ነገር ተከስቷል ማለት ሳይሆን እየተለቀች ስለሆነ እንደልቧ ለመንቀሳቀስ ቦታ ስለማታገኝ ነው። በተያያዘ ልጅሽ ለመወለድ የሚያስፈልጋትን አቀማመጥና ቦታ መያዝ ትጀምራለች።
አንገቷን ማዟዟር፣ እጅና እግሯን ማንከሳቀስ በደንብ ትችላለች። እንቅስቃሴዋ ጠንካራ በመሆኑ ልትረብሽሽ ትሽላለች ነገር ግን ጤነኛና ጠንካራ የመሆኗ ምልክት ነውና ብዙም አይክፋሽ። አጥንቷም በደንብ እየጠነከረ ሲሆንየጭንቅላቷ አጥንት ግን ለስላሳና በደንብ ያልገጠመ ይሆናል። ይህም በወሊድ ጊዜ ጭንቅላቷ እንዲወጣ ያደርጋል። በወሊድ ጊዜ ለመውጣት በምታረገው ጥረት ጭንቅላቷ ላይ የሚፈጠረው ጫና የጭንቅላቷን ቅርፅ ሞላላ ሊያደርገው ይችላል። ይህ መጠፎ ነገር አደለም – የልጆች ጭንቅላት የሚጠነክረውና መልኩን መያዝ የሚጀምረው አመት ካለፋቸው በኋላ ነው። አራስ እንዳሉ ሲተኙ ጭንቅላታቸውን በማዟዟር ቅርፁን ማስተካከል ይቻላል።
በወሩ መጨረሻ
  • ከ 2 እስከ 2.4 ኪሎ ግራም ትመዝናለች
  • 46 ሴንቲ ሜተር ትረዝማለች
  • በአይን ብትታይ ሐብሐብ ታክላለች።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ