ስለእናት

አብዛኛዎቹ ነብሰ ጡሮች ስድስተኛ ወር በደንብ ምቾት ያለው እንደሆነ ይመሰክራሉ። የድካምና የማቅለሽለሽ ስሜቱ አለመኖር ጉልበትን በመስጠት ልጅሽን ስለምታይበት ቀን እንድትጓጊ ያረጋል። የልጅሽን መምጣት አስመልክቶ ግን አንቺ ብቻ ሳትሆኚ ሰውነትሽም ልጅሽ ከማህጸን ውጪ ለሚጠብቀው ህይወት እንዳይበርደው ውፍረቱን እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ ማለት አንቺም ክብደትሽ በፍጥነት መጨመር ይጀምራል ማለት ነው – በአበዛኛው 0.5 ኪሎ በሳምንት ትጨምሪያለሽ። ምንም እንኳን ክብደት መጨመርሽ የተፈጥሮ ሂደት ቢሆንም ከሱ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የወገብና የእግር ህመም ሊያስቸግርሽ ይችላል። ካልሲየምና ፖታሲየም ያላቸው ምግቦች – እንደ ወተትና ሙዝ – ለአጥንት ጥሩ በመሆናቸው አዘውትረሽ ተመገቢ።
ይሄ ወር ካለቀ በኋላ የሚወለዱ ልጆች ያለጊዜያቸው ቢወለዱም የመኖር እድላቸው ሰፊ በመሆኑ ይህን ወር መጨረስ ማለት ቀላል የምስራች አደለም። ቢሆንም ልጅሽ ማህፀን ውስጥ የምትቆይበት እያንዳንዱ ቀን ለመኖሯ ዋስትና እየሰጠ ስለሚሄድ ሁሌም እራስሽን በደንብ ጠብቂ። ከ 37 ሳምንት በፊት የሚወለዱ ልጆች ያለጊዜያቸው የተወለዱ ህፃናት ሲባሉ እነዚህ እፃናት በአብዛኛው ጊዜ ከሰባተኛ ወር ጀምሮ ስለሚወለዱ ያለጊዜው የሚመጣን የምጥ ምልክት ከአሁን ጀምሮ ማወቅ ተገቢ ነው። ህፃናት ያለጊዜያቸው የሚወለዱት አስገዳጅ ምክንያቶች ካሉና ሃኪም ከወሰነ ወይም ደሞ ያለጊዜው ምጥ ሲጀምር፣ የእንሽርት ውሃ ሲፈስ፣ ወይም ማህፀን ምጥ ሳይኖር መከፈት ከጀመረ ነው። ያለጊዜው መውለድ በሚል እርእስ የተፃፈውን መረጃ በደንብ አንብቢ።
ሰውነትሽን በተመለከተ ከሰውነት ውፍረትና ከጡት መጠን መጨመር በተጨማሪ በዚህ ወር የተለያዩ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። ወፍራምና አንፀባራቂ ፀጉር፣ ፀጉር በየቦታው ማብቀል፣ ቶሎ ቶሎ ጥፍር ማብቀል፣ የቆዳ መጥቆር፣ የቆዳ መሰነጣጠቅ፣ የጡት ጫፍ መተለቅና መጥቆር እንዲሁም የእግር መጠን መጨመር የተለመዱ የእርግዝና ክስተቶች ናቸው። አትጨነቂ ከውበት በዘለለ ባንቺም በፅንሱም ላይ ምንም ጉዳት አያደርሱም። ፀጉርሽ የሚበዛውና የሚያምረው ብዙ እያበቀልሽ ሳይሆን መነቃቀል ስላቆመ ነው – የእርግዝና ሆርሞኖች የሚሰጡሽ ብቸኛ ጥቅም መሆኑ ነው። ስትወልጂ በፍጥነት በመነቃቀል ስለሚቀንሱ እስካሉ ድረስ አግጪባቸው።
  • ቀለበት የምታደርጊ ከሆነና እጅሽ እየወፈረ ወይም እያበጠ ከሆነ ሳይረፍድ በፊት አውልቂያቸው። ካንቺ እንዲለዩ የማትፈልጊያቸው ቀለበቶች ከሆኑ አንገትሽ ላይ ማንጠልጠል ይመረጣል።
የእግር እብጠት ካለ መከላከያ መንገዶችን ተጠቀሚ ግን ከሚገባው በላይ ከሆነ እብጠቱ የፕሪ-እክላምዚአ ምልክት ሊሆን ስለሚችል ህክምና ማግኘት ይኖርብቻል። ከ 24-28 ባለው ሳምንት ውስጥ የስኳርና የቀይ ደም ሴል ብዛትሽ ይለካል። ይህም ምርመራ ችግር ካለ አስቀድሞ ለመቆጣጠር ይረዳል። የስኳር መጠንሽ ከፍተኛ መሆን የልጅሽን መጠን በጣም በመጨመር -በተለይ ከወገብ በላይ – በምጥ መውለድን ሊያከብድብሽ አልፎም በቀዶ ጥገና እንድትገላገዪ ሊያደርግሽ ይችላል። የቀይ ደም ሴል ማነስም የራሱ የሆኑ ችግሮችን ያስከትላል። የእርግዝና ውስብስብ ችግሮች ብለን የዘረዘርናቸውን ማንበብ ይኖርብሻል።

ስለፅንሱ

በዚህ ወር ልጅሽ በጣም ከመንቀሳቀሷ የተነሳ ስትገላበጥና ስትራገጥ ከመሰማት አልፎ ማየት ትችያለሽ። የለመደቻቸውን ሰዎች ድምፅ ስትሰማም እንቅስቃሴ በማረግ መልስ ትመልሳለች። የማዳመጥ አቅሟ በመጨመሩ በጣም የሚጮሁ ድምፆችን ትለምዳቸውና ከተወለደችም በኋላ መስማቱ አያስደነግጣትም።
የልብ ምቷም በጣም ስለሚጠነክር ሆዶሽን በደንብ ላዳመጠ ሰው መሰማት ይችላል። ቆዳዋ አሁንም ስስ ሆኖ ወደ ውስጥ ቢያሳይም ከለሯ ግን ቀስ በቀስ መልኩን እየያዘ እየመጣ ነው። አሁን ከሞላ ጎደል ትንሽዬ አራስ ልጅ ብትመስልም ማየት ቢቻል ቆዳዋ በጣም ስስ ከመሆኑ ቀዳዳዎቹን እና ሰውነቷን የሸፈነውን ፀጉር ማየት ይቻላል። የእንሽርት ውሃውን እንደ አየር ወደ ውስጥ ማስገባትና ማስወጣት ትጀምራለች። ይህም ስትወለድ ለምትስበው ለመጀመርያ አየር እንድትዘጋጅ ይረዳታል።

በወሩ መጨረሻ
  • ከ 750 እስከ 900 ግራም ትመዝናለች
  • 36 ሴንቲ ሜተር ትረዝማለች
  • በአይን ብትታይ ዝኩኒ ታክላለች።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ