ስለእናት

በዚህ ወር በምታረጊው የቅድመ ወሊድ ክትትል ቀጠሮ ላይ እንደ እናት ማሰብ እንድትጀምሪ ከሚያረጉሽ ነገሮች አንዱ የልጅሽን የልብ ድምፅ በአልትራ ሳውንድ ምርመራ ጊዜ ማዳመጥ መቻልሽ ነው። በፍጥነት የሚመታ ጠንካራ የከበሮ ምት ሊመስልሽ ይችላልይህ በሂዎትሽ ከሰማሻቸው ድምፆች በሙሉ ውብ የሆነው ድምፅ ነው።
አሁን እርግዝናሽ እርግጥ ከመሆንም አልፎ አስጊ የሚባለዉን ጊዜ አልፈሽዋል። ይህ ማለት 3 ወር ከሞላሽ ፅንሱ የመውረድ እድሉ በጣም አናሳ ነው። ከፈለግሽ አሁን የእርግዝናሽን ዜና ለቤተሰብና ለወዳጅ ዘመድ ማካፈል ትችያለሽ። እርግዝናሽ እርግጥ ሲሆን ስለገንዘብ አያያዝሽ ማሰብ መጀመር አለብሽ ግን ጭንቀት ውስጥ ሊከትሽ አይገባም። ጭንቀትሽን የሚያቀልልሽ ከሆነ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችን ቀስ በቀስ መግዛት መጀመር ትችያለሽ። በመውለጃሽ ሰአት ሁሉንም በአንዴ ከመግዛት የተሻለም ነው። የመጀመርያዎቹ ሶስት ወራቶች እየተጠናቀቁ በመሆኑ የድሮ ማንነትሽ ሊመለስ ይችላል። ሆኖም ሆርሞኖች ስሜታዊና አካላዊ ለውጦችን ያመጣሉ። ራስ ምታት፣ የፀባይ መለዋወጥ፣ ማቅለሽለሽና ድካም የተለመዱ ናቸው። የምግብ አምሮትና ቶሎ ቶሎ መሽናት ይህን ወር ጨምሮ ወደፊትም እየተጠናከሩ ይሄዳሉ። ቃርና የሆድ ድርቀትም በዚህ ወር ከሚታዩ የእርግዝና ምልክቶች ውስጥ ይገኛሉ።
  • የምግብ አምሮትሽ ከምግብ ነገሮች ውጪ ለምሳሌ እንደ አፈር መብላት ከሆነ ሀኪምሽን አማክሪ።
በዚህ ወር እስከ 2 ኪሎ ልትጨምሪ ትችያለሽ። ዳሌሽ ቢሰፋም እርጉዝ የመምሰል እድልሽ በጣም ጠባብ ነው – የእርጉዝ ልብስ መልበስ ላይም አያደርስም። እርግዝናሽ ተጀምሮ እስቂያልቅ ድረስ እንቅስቃሴ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።  እንቅስቃሴ ማድረግ ሰውነትሽ ፅንሱን የመሸከም ጥንካሬ እንዲኖረው፤ ምጥን ለማቅለልና ከወሊድ በኋላ ቶሎ ክብደት እንድትቀንሺ ለማድረግ ይረዳል። አሁን የልጅሽ አጥንት መጠንከር ስለሚጀምር ካልሲየም ያለው ምግብ አዘውትሪ – ወተት እርጎ የመሳሰሉትን።

ስለፅንሱ

ከባለፈው ወር ሲነፃፀር የተሻለ ሰው ይመስላል – እጁ፣ እግሩ፣ ጣቶቹና የፊቱ ገፅታው በተሻለ ቦታቸውን ይይዛሉ። ሰውነቱ በፍጥነት እያደገ መሆኑ ከጭንቅላቱ ጋር ያለውን የመጠን ልዩነት ያጠበዋል። ጆሮውና አፍንጫውም ወደ ውጪ መብቀል ጀምሯል። አይኑ ሙሉ ለሙሉ ቢኖርም እስከ 27 ሳምንት ድረስ እንደተከደነ ይቆያል። ሁለተኛው ወር ላይ የነበረውም ጭራ መሳይ አካል ይጠፋል።
ንቁ በመሆን ለነገሮች  መልስ መመለስ ይጀምራል። ለምሳሌ በእጅሽ ሆድሽን ብታሻሺ ወደ እጅሽ ይጠጋል።  እጅና እግሩን ማንቀሳቀስ ቢጀምርም ላንቺ እስኪታወቅሽ ድረስ ግን ጊዜ ይወስዳል። ወንድም ሆነ ሴት ፆታዊ አካላቸው የተሰራ ሲሆን በበቂ ሁኔታ አድጎ ለመታየት ግን ሌላ 2 ወር ያስፈልገዋል። ሴት ከሆነች የዘር እንቁላሏ ካሁኑ ዝግጁ ይሆናል – ብዛቱም እስከ 1.2 ሚሊዮን ይሆናል።
እትብቱ ውስጥ ማደግ የጀመረው ሆድቃ ወደ ሆዱ ይገባል። ኩላሊቱ፣ አንጀቱ፣ አይምሮውና ጉበቱ ስራቸውን ቢጀምሩም ማደጋቸውን ግን ይቀጥላሉ። ስርአተ ማጣሪያው መስራት በመጀመሩም ሽንት ይሸናል። ይህ ሽንት ወደ እንሽርት ውሃው ሲሆን የሚገባው የእንግዴ ልጁ አደጋን እንዳይፈጥር ሽንቱን መልሶ ያጣራል።

በወሩ መጨረሻ
  • ከ 28 እስከ 30 ግራም ይመዝናል
  • 4 ሴንቲ ሜተር ይረዝማል
  • በአይን ቢታይ የአተር ፍሬ ያክላል
Share on facebook
Share on google
Share on twitter
መዝጊያ