ስለእናት

የልጅሽን ፆታ ለማወቅ ጓግተሽ ከሆነ ይህ ወር ደስ የምትሰኝበት ጊዜ ነው። አዎ የልጅሽ ፆታ ከ 20ኛው ሳምንት ጀምሮ በአልትራሳውንድ መታየት ይጀምራል። ታድያ የልጅሽን ፆታ ማወቅሽ ስለስሙ፣ ስለምትገዥለት ልብስ፣ ስለምታጫውችው ጨዋታ እያሰብሽ ዘና እንድትይ ያረግሻል። በተጨማሪም እንቅስቃሴው በደንብ ይታወቅሻል። ለመጀመርያ ጊዜ የልጅሽን እንቅስቃሴ መስማት ወደር የሌለው ደስታን ሲሰጥ እስክትለምጂው ድረስ በተንቀሳቀሰ ቁጥር ብርቅ ይሆንብሻል። አዎ ሴት በመሆንሽ የተሰጠሽ ፀጋ ነውና ተደሰቺ።
በሌላ በኩል እስከ 6ኪሎ ክብደትሽ ስለሚጨምርና ሆድሽ ስለሚገፋ ልብሶችሽ እንደድሮ ምቾት አይሰጡሽም። ክብደትሽን መከታተል ቢኖርብሽም ብዙ ሊያስጨንቅሽ ግን አይገባም። ማተኮር ያለብሽ ተመጣጣኝ ምግብ መብላትሽ ላይና በቂ እንቅስቃሴ ማረግሽ ላይ ነው። የምግብ አምሮትሽ እንደጉድ ቢጨምር አይግረምሽ – የምትበይው ለሁለት ሰው መሆኑን አትርሺ። የልጅሽ አይምሮ በደንብ ማደግ የሚጀምርበት ወር ስለሆነም አሳ መብላት ብታዘወትሪ በጣም ጥሩ ነው። ከክብደትሽ ጋር ተያይዞ የወገብና እግር ህመም ይጀምርሽ ይሆናል (ማቅለያ መንገዶችን ተግብሪ)። ነገሮችን መርሳትና እንደድሮ አጣርቶ አለማሰብ በዚህ ወር የተለመደ ነው። ህይወትሽን ለማቅለል እቃዎችን ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ቦታ ማስቀመጥና እቅዶችሽን በማስታወሻ መያዝ ይመከራል።
ልጅሽ በፍጥነት እያደገ በመሆኑና ሰውነትሽ ለልጅሽ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማቅረብ ብዙ ስለሚለፋ የደም ግፊትሽ ይቀንሳል። ተያይዞም የማዞር ስሜት ሊኖር ስለሚችል ተቀመጠሽ ወይም ተኝተሽ ስትነሺ ረጋ ብለሽ መሆን አለበት። በምንም መልኩ የመዝለል እንቅስቃሴ ማረግም የለብሽም። ስራ ሰርተሽ ስታርፊ ወይ ተኝተሽ ስትገላበጪ የውጋት ስሜት ሊኖር ይችላል። ይህ የውጋት ስሜት አርፈሽበት ካልተወሽ ወይም እየባሰ ከመጣ ሀኪምሽን አማክሪ።
ሆድሽ ላይ ከእንብርትሽ ጀምሮ ወደታች የሚወርድ ጥቁር መስመር ብታይ አትጨነቂ። ሁሉም ነብሰ ጡር ላይ ከ5 እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ይወጣል። በሌላ በኩል ግን ቆዳሽ እየተለጠጠ በመሆኑ የቆዳ መሰንጠቅ ሊያጋጥምሽ ይችላል። ቶሎ ቶሎ ገላን በመታጠብና ሎሽን በመቀባት ማሳከኩን መቀነስ ይቻላል። ስትተኚ በተቻለሽ መጠን በጎን መተኛት ማህጸንሽ የደም ትቦሽ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ይቀንሳል። በጎን ስትተኚ ከጀርባሽ፣ ጎንሽ ስር ወይም እግርሽ ስር ትራስ በማረግ ምቾትሽን ጠብቂ።
በዚህ ወር የቅድመ ወሊድ ክትትል ቀጠሮ አልትራ ሳውንድ መነሳት ግድ ነው። ይህ የልጅሽን ፆታ ለማወቅ፤ እድገቱ ጤነኛ መሆኑን ለማረጋገጥ፤ የፅንሱንም ሆነ የእንግዴ ልጁን አቀማመጥ ለማየት፤ ስንት ልጅ እንዳረገሽና የወሊድ ቀንሽን በእርግጠኝነት ለማወቅ ይረዳል። ስራ የምትሰሪ ከሆነ ከወለድሽ በኋላ ልጅሽን የሚይዝልሽ ሰው ማፈላለግ ተገቢ ነው። ከወለድሽ በኋላ ልጅሽን ለማታቂው ሰው ከመስጠት አስቀድመሽ ሰው መፈለግና መቅጠር ጠባቂዋን በደንብ እንድታቂያትና እንድትላመዱ ያደርጋል። ብዙ አብሮ መቆየትም የቤተሰብነት ስሜትን እንዲፈጥርና እንደራሷ ልጅ ዕንድትንከባከበው ይረዳል። የህፃናት ማቆያ ለመስጠት ከሆነም ሃሳብሽ ጥሩ የሚባሉትን መጎብኘትና ምርጫሽን ማስተካከል ተገቢ ነው።

ስለፅንሱ

ስቅታና ማዛጋት የቀን ተቀን ተግባሩ ነው። ምንም እንኳን አይኑ የተከደነ ቢሆንም ብርሃንን ግን በደንብ ይለያል – ጭለማ ውስጥ ስትሆኚም በደንብ ያቃል። ሆድሽ ላይ መብራት ብታበሪ ወይ ፊቱን ያዞራል ወይ በእጁ ፊቱን ይከልላል። ይህ ብቻ አደለም አሁን ያንቺን ድምፅና የልብ ምትሽን በደንብ ያቀዋል። አባቱ ሆድሽን ቀርቦ የማውራትና ልጁን የማጫወት አመል ካለውም ያባቱን ድምፅ በደንብ ይለያል። አዎ አሁን በደንብ ማዳመጥ ይችላል። ልጆች አብዛኛውን ነገር የሚለምዱት በማህጸን እያሉ በመሆኑ ባለሽ ጊዜ ሁሉ አዋሪው፣ ዝፈኚለት፣ ተረት አውሪለት።
ሴት ከሆነች እንቁልጤዋና የዘር ትቦዋ ዝግጁ ሲሆን የውጪኛው የብልት ክፍሏም ማደግ ይጀምራል። ወንድ ከሆነ ደሞ ብልቱ ወደውጪ ያድጋል – ለዛም ነው በአልትራሳውንድ ፆታ መለየት የሚቻለው። እጅና እግሩ በበቂ ሁኔታ አድጎ ከቀረው ሰውነቱ ጋር በመጠን ተስተካክሏል። ቆዳው በውስጥ በኩል በቅባት ይሸፈናል። ይህ በአራስነት ወቅት እራሱን ከብርድ የሚከላከልበት መንገድ ነው።
የእንሽርት ውሃውን በተደጋጋሚ በመዋጡ የማጣርያ ስርአቱ በደንብ እንዲሰራ ያደርገዋል። በዚህም የማጣራት ሂደት ከተወለደ በኋላ የሚወጣውን የመጀመርያ ሰገራ ከሚውጠው የእንሽርት ውሃ ውስጥ ያጣራል። ይህ ሰገራ በከለሩ ጥቁርና ዝልግልግ ያለ ነው። አጥንቱ በበቂ ሁኔታ በመጠንከሩ የደም ህዋስ ማምረት ስራውን ከጣፊያ ይረከባል።

በወሩ መጨረሻ
  • ከ340 እስከ 350 ግራም ይመዝናል
  • 27 ሴንቲ ሜተር ይረዝማል
  • በአይን ቢታይ ካሮት ያክላል
  • ልብ በይ ከባለፈው ወር ቁመቱም ክብደቱም በእጥፍ ጨምሯል። ከዚህ በኋላም እድገቱ በጣም ፈጣን ይሆናል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ