ስለእናት

ይህ ወር ምቹ የሚባለው ወር ስለሆነ ለራስሽ ጊዜ በመስጠት ዘና ለማለትና እርግዝናሽን ለማጣጣም ሞክሪ። አካላትሽ ላይ የሚኖሩት ለውጦች (ጡትሽ ዳሌሽ መቀመጫሽ) ውበትን ስለሚያጎናፅፉ ጥሩ ስሜት እንዲሰማሽ ያረግሻል። አብዛኛው ነብሰ ጡሮች ፊታቸው ጥርት የማለትና የማብራት ስሜት ሲያሳዩ የተወሰኑ ነብሰ ጡሮች ላይ ግን የመትቆርና ነጠብጣብ ወይም ማዲአት ማውጣት ይታያል። ጥቁረቱም ይሁን ማዲአቱ በጊዜ የሚለቁ ናቸው።
ዘጠኝ ወር ሙሉ ከሚያማችው ነብሰ ጡሮች መካከል ካልሆንሽ በስተቀር በዚህ ወር ማቅለሽለሽና ድካም የሚባሉት ምልክቶች ይቀንሳሉ ወይም ይጠፋሉ። የሆድ ድርቀቱ ግን ሊከፋ ስለሚችል እንቅስቃሴ ማድረግ፤ ብዙ ውሃ መጠጣት፤ ፍራፍሬና ቅጠላ ቅጠል መብላት አትዘንጊ – ቀለል ያረግልሻል። የአፍንጫ መዘጋትና መድማት በዚህ ወር ሊከሰቱ ከሚችሉ የእርግዝና ጣጣዎች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው። በጣም ካስቸገረሽ ሀኪምሽን አማክሪ። ቃሩም እየባሰ ስለሚመጣ ማቅለያ መንገዶችን መተግበር አትርሺ። የብልት ፈሳሽሽ ሊጨምር ይችላል የተለመደ ነው።
ሰፋፊ ልብስ የምትለብሺ ከሆነ እስከ 6 ወር መግቢያሽ ሰው ላያቅብሽ ቢችልም በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ላንቺ የሆድሽ መጠን መተለቁ በደንብ ይታወቅሻል። ታድያ ሆድሽ እየገፋ ሲመጣ በጎንሽ መተኛት ይኖርብሻል – በተለይ በግራ ጎንሽ። በጎን መተኛት የደም ዝውውርሽንበማፋጠን ለልጅሽ አስፈላጊ ነገሮች በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ ያደርጋል። የሆድሽ መግፋት ሚዛንሽን ስለሚያዛባው ታኮ ጫማ ባታረጊና እንቅስቃሴ ስታደርጊ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ቢሆን ይመከራል።
በቅድመ ወሊድ ክትትልሽ ወቅት የስኳር መጠንሽ ይለካል። ስኳር ካለብሽ በተቀረው የእርግዝና ጊዜሽ የአመጋገብ ባህልሽን በደንብ ማስተካከል ይኖርብሻል። ሌላ ልብ ልትይው የሚገባሽ ክብደትሽን ነው። በእርግዝና ሰአት ልትጨምሪው የሚገባ የክብደት መጠን አለ። ይህ የክብደት መጠን እርግዝናው ሲጀመር በነበረሽ ክብደት ሲወሰን – ከማርገዟ በፊት ክብደቷ መካከለኛ የነበረች አንድ ነብሰ ጡር ከ11 እስከ 16 ኪሎ መጨወር ይኖርባታል። የመጀመርያ ሶስት ወራቶች ላይ ክብደትሽ እስከ 2 ኪሎ ብቻ ሲጨምር በተቀሩት ወራቶች ግን በየሳምንቱ ወደ ግማሽ ኪሎ ገደማ ትጨምሪያለሽ። በእርግዝና ወቅት ከመጠን በላይ መወፈርም መክሳትም የራሱ የሆነ ጉዳት ስላለው በጣም እየወፈርሽ ወይም እየከሳሽ ከሆነ ወይም እርግዝናውን ስትጀምሪ በጣም ቀጭን ወይም ወፍራም ከነበርሽ ሀኪምሽን አማክሪ። የአመጋገብና እንቅስቃሴ የማድረግ ባህልሽን እንደ ክብደትሽ መጠን እንድታስተካክዪ ይደረጋል።
ምንም እንኳን ብዙ ወራት ቢቀርሽም ለልጅሽ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ማዘጋጀት ሊያስደስትሽ ይችላል – ለምሳሌ ልብስ መግዛት፤ የቤት እቃ አቀማመጥሽን መቀያየር፤ የሚተኛበትን ክፍል ወይም ቦታ ማዘጋጀት። ይህን ማድረግ ክፋት ባይኖረውም ከአቅምሽ በላይ የሆኑ ስራዎችን መስራት ልጅሽን ሊጎዳ ብሎም ውርጃን ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማረግ ይኖርብሻል።

ስለፅንሱ

ከባለፈው ከሌላው ሰውነቷ ጭንቅላቷ አሁንም በአንፃሩ ትልቅ ቢሆንም ቅንድብና ሽፋሽፍት በማብቀል ስትወለድ ወደሚኖራት መልክ ትጠጋለች። ከጭንቅላቷ ውጪ ያሉ አካላቶቿም በፍጥነት ያድጋሉ። አንገቷ ስለሚያድግም ጭንቅላቷ ከሰውነቷ ተለይቶ አንገቷ ላይ ይቀመጣል። እንደ ማዛጋት፣ መዋጥና እጅ መጥባት የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችን ታደርጋለች። የልብ ምቷም ስለሚጠነክር በልብ ማዳመጫ መደመጥ ይችላል።
እጇ ከሰውነቷ ጋር የተስተካከለ ቁመት ሲኖረው እግሯ በፍጥነት በማደግ ከእጇ በቁመት ይበልጣል። ሰውነቷ ጸጉር ያበቅላል – መወለጃዋ ሲቃረብ የሚረግፍ ፀጉር ነው። ጉበቷ ቅባት ለመፍጨት የሚያገለግለዉን የጉበት ፈሳሽ (ባይል) ጣፍያዋ ደሞ ቀይ የደም ህዋሶችን ያመርታል። እጅና እግሯ በፍጥነት በማደጉና አጥንቶቿ በመጠንከራቸው በደንብ ትንቀሳቀሳለች። አንዳንድ ነብሰ ጡሮች ፅንሱ ሲንቀሳቀስ የእርግብግቢት አይነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሰውነቷ እያደገ በመጣ ቁጥር ታዲያ እትብቷም እየረዘመና እየወፈረ ይመጣል።

በወሩ መጨረሻ
  • ከ140 እስከ 150 ግራም ትመዝናለች
  • 13 ሴንቲ ሜተር ትረዝማለች
  • በአይን ብትታይ ቀይስር ታክላለች
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ