ስለእናት

በህክምና እርግዝና የሚቆጠረው ለመጨረሻ ጊዜ የወር አበባ ማየት ከጀመርሽበት ቀን አንስቶ ሲሆን የምትወልጂበት ቀንም ከዚህ ቀን አንስቶ ከ 40 ሳምንት በኋላ ይሆናል። ይህ የሚደረገው እርግዝና የሚፈጠርበት ትክክለኛው ቀን ስለማይታወቅና ቀኑም እንደየሰዉ ስለሚለያይ ነው። ይህም ማለት በመጀመርያው የእርግዝና ወር የመጀመርያ ሁለት ሳምንታት ገና እርግዝና አልተፈጠረም እንደማለት ነው። በየ 28 ቀን ውስጥ የወር አበባ የምታይ ሴት ወሩ በገባ ከ 9-21 የማርገዝ እድል ይኖራታል። በአብዛኛው ጊዜ ግን በወሩ አጋማሽ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም መሰረት የዘር መቋጠሪያሽ የሴት ዘር ይለቃል። ይህ በሆነ በ 24 ሰአት ውስጥ ግብረስጋ ግንኙነት ካደረግሽና የወንድ ዘር ካገኘ ወደ ፅንስነት ይቀየራል።
ይህ ወር ታድያ እርግዝና የሚፈጠርበት እንጂ እርጉዝ መሆንሽን የምታቂበት ጊዜ አይደለም። ለመውለድ አቅደሽ ግብረስጋ ግንኙነት አርገሽ ከሆነ ግን እርግዝና መከሰቱን አስመልክቶ ሊታዩ የሚችሉ ለውጦችን መከታተል ትችያለሽ። ሆኖም እርግዝና እርግጠኛ የሚሆነው በምርመራ ሲሆን የወር አበባሽ ከቀረ ከ 5 ቀናት በኋላ በሽንት ምርመራ መለየት ይቻላል።

ስለፅንሱ

እርግዝና ለመፈጠር የሴት ዘር በተለቀቀ በ 24 ሰአት ውስጥ የወንድ ዘር ማግኘት አለበት። ይህ ሲሆን ፅንስ ይፈጠራል። የወንዱ ዘር ኤክስ (X) ከሆነ ሴት ዋይ (Y) ከሆነ ወንድ ልጅ ይፀነሳል። ፅንስ የሚፈጠረው በሴት የዘር ትቦ ውስጥ ሲሆን ወደ ማህፀን ለመድረስ ከ 3-4 ቀን ይፈጅበታል። በዚህም ጉዞ ከ 1 ወደ 16 ህዋስ ይባዛል። ማህፀን ከደረሰ 1 ወይ 2 ቀናት በኋላ ከማህፀን ጋር ይጣበቃል በዛውም እድገቱን ይጀምራል። በዚህ ሰአት ፅንሱ ሽል ሲባል ወደፊት ሲያድግ ወደሰውነቱ፣ እንግዴ ልጅና የእንሽርት ውሃ የሚቀየሩ ህዋሶችን የያዘ ይሆናል።
የእንግዴ ልጅ ህዋሱ ኤች ሲ ጂ (HCG) የሚባል ሆርሞን በመልቀቅ የዘር ትቦው ሌላ እንቁላል እንዳይለቅና የእርግዝና ሆርሞኖች እንዲለቀቁ ያደርጋል። እነዚህ የእርግዝና ሆርሞኖች (Estrogen and Progesterone) የማህፀን ግድግዳ እንዳይፈርስና የወር አበባ እንዳይመጣ ይከላከላሉ። ኤች ሲ ጂ (HCG) ከዛም ባለፈ በሽንት ምርመራ ጊዜ እርግዝናን ለማወቅ ይረዳል። የእንግዴ ልጁ ዝግጁ እስኪሆን ድረስ ምግብና አየር በጥቃቅን ትቦዎች ይቀበላል። በወሩ መጨረሻ ግን የእንግዴ ልጁ ይህን ስራ ተረክቦ ለተቀሩት 8 ወራት ምግብና አየርን በእትብቱ በኩል ያመላልሳል።
ከ 4ኛው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ 10 ሳምንታት ውስጥ የልጅሽ አካላቶች በሙሉ ተሰርተው ሲያልቁ አንዳንዶቹ ስራም ይጀምራሉ። ይህ ጊዜ ለልጅሽ እድገት መሰረታዊ ጊዜ ነውና ለምታደርጊው፣ ለምትበይውም ሆነ ለምትጠጪው ነገር ትንቃቄ ያስፈልጋል። በወሩ መጨረሻ ጥቁር አዝሙድ ያክላል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ