ከማህፀን ውጪ እርግዝና

ከማህፀን ውጪ እርግዝና የሚከሰተው ፅንስ ከማህፀን ግድግዳ ውጪ በየትኛውም ቦታ በሚያድግበት ወቅት ነው። ይህ የሚሆነው በማህፀን ትቦ ውስጥ የተፈጠረው ፅንስ ወደ ማህፀን በተገቢው ጊዜና ሁኔታ መተላለፍ ሲያቅተው ነው። አብዛኛው የሚከሰተው በማህፀን ትቦ (የሴት ዘር መተላለፊያ ትቦ) ውስጥ ቢሆንም አልፎ አልፎ በእንቁላል ማቀፍያ (እንቁልጤ)፣ በማህፀን አንገት ላይ እንዲሁም በሆድ እቃ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ይህ ያለቦታው ያደገ ፅንስ በትክክለኛ መንገድ ስለማያድግና የእናትየውን አካል ስለሚጎዳ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ አይችለም። እርግዝናው ሊያመጣ የሚችለውን አስከፊ ጉዳት ለመከላከል ህክምና ማግኘት ተገቢ ሲሆን በጊዜ ህክምና ማድረግ ቀጥሎ የሚከሰተዉን እርግዝና ጤናማ የማድረግ እድል ያሰፋል። ሌላ ቦታ ያደገን ፅንስ ወደ ማህፀን ማስተላለፍ ስለማይቻል ፅንሱ መቋረጥ ይኖርበታል።
ከማህፀን ውጪ እርግዝና

ምልክቶች

ከማህፀን ውጪ እርግዝና ፅንስ እንደተፈጠረ የሚከሰት በመሆኑ በመጀመርያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ነብሰ ጡር መሆንሽን ሁላ ላታውቂ ትችያለሽ። የተለየ ምልክት የማሳየት እድሉም በጣም ጠባብ ነው። ነብሰ ጡር መሆንሽ ከተረጋገጠም በኋላ ከተለመዱ የእርግዝና ስሜቶች ውጪ የተለየ ነገር ላይታይብሽ ይችላል። ቀን እየገፋ፣ ፅንሱ ማደግ እያቃተውና የማህፀን ትቦሽን እየጎዳው ሲመጣ ግን ከስር የተዘረዘሩትን ምልክቶች ማየት ትጀምርያለሽ:
 • በአንድ ጎን የሚሰማ የሆድ ወይም የማህፀን ህመም፤ የመውጋት የመቁረጥ ስሜት፤ የሆድ ማበጥና መጠንከር። ህመሙ በእንቅስቃሴ ጊዜ፣ ሽንት ቤት በምትቀመጪና በምታስይ ጊዜ የሚጨምር
 • ቀላል የደም መፍሰስ
 • የማህፀን ትቦ ከተቀደደ ማዞር፣ እራስን መሳት፣ ትከሻ አንገትና ፊንጢጣ ላይ ህመም፣ እንዲሁም ለሒዎት የሚያሰጋ ብዛት ያለው የደም መፍሰስ ያስከትላል
✸ ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች ከታዩብሽ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ይኖርብሻል።

ማንን ያጠቃል

 • ማንኛውም የማህፀን፣ የማህፀን ትቦ እና የሆድ እቃ ቀዶ ጥገና ያረገችን ሴት
 • በማህፀንና በማህፀን ትቦ ላይ ቁስለት ካለ
 • የማህፀን ትቦ ቅርፅ ትክክል ካልሆነ
 • በእርግዝና ሰአት እድሜ ከ 35 አመት በላይ ከሆነና በተለይ የመጀመርያ እርግዝና ከሆነ
 • ተመሳሳይ እርግዝና አስቀድሞ ተፈጥሮ ከነበር
 • ተደጋጋሚ ውርጃ ያደረገች ከሆነ
 • የአባላዘር በሽታ ካለባት
 • እርግዝናው በማህፀን የሚቀበር (አይ ዩ ዲ) የእርግዝና መከላከያ እየተጠቀምሽ ከተፈጠረ
 • የምታጨስ ነብሰ ጡር

ህክምና

ከማህፀን ውጪ የተፈጠረን እርግዝና ለማወቅ አስችጋሪ ቢሆንም የቅድመ ወሊድ ክትትል ለምታረግ ነብሰ ጡር በጊዜ የመታወቅ እድሉ ሰፊ ነው። በመጀመርያው የቅድመ ወሊድ ህክምናሽ ላይ ሆድሽ ሲነካ የሚያምሽ ከሆነ ወይም ዶክተርሽ እብጠት ሆድሽ ላይ ከታየው ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ እርግጠኛ ለመሆን ይሞከራል። አልትራሳውንድ በመጠቀምም የፅንስ አቀማመጡ ትክክል መሆኑን ማወቅ ይቻላል።

ፅንሱ ከማህፀን ውጪ ከሆነ መቋረጥ ስለሚኖርበት የእርግዝና ጊዜሽ ታይቶ መዳኒት ይሰጥሻል ወይም ቀዶ ጥገና ይደረግልሻል። ፅንሱ ካልገፋና የማህፀን ትቦሽን ካልቀደደው መዳኒቱ የእንግዴው ልጅ እንዳያድግ በማድረግ የፅንሱን እድገት ይገታል። ፅንሱም በጊዜ ሂደት ከሰውነትሽ ጋር ይዋሃዳል። እርግዝናሽ ከገፋ፣ አስከፊ ህመም ላይ ካደረሰሽ፣ ደም በብዛት እየፈሰሰሽ ከሆነ ወይም የማህፀን ትቦሽ መወገድ ካለበት ቀዶ ጥገና ማድረግ ግዴታ ይሆናል። መዳኒትም ወሰድሽ ቀዶ ጥገና አደረግሽ ድጋሚ ለማርገዝ ቢያንስ 6 ወር መጠበቅ ይኖርብሻል። አንድ ሴት ሁለት የማህፀን ትቦ ስላላት አንደኛው በቀዶ ጥገና ቢወጣም በሌላኛው የማርገዝ እድል አላት።

Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ