ክትባት

በኢትዮጵያ ያለው መደበኛ የክትባት መርሀ ግብር (EPI) ስምንት ክትባቶች ያካትታል። የኦፒቪ (OPV) ክትባት የልጅነት ልምሻን ለመከላከል፣ ቢሲጂ (BCG) የሳንባ ነቀርሳን ለመከላከል፣ የፀረ አምስት (DPT – HepB – Hib) ደግሞ ዘጊ አናዳ፣ ትክትክ፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ የጉበት በሽታ፣ የሳምባ ምችና ማጅራት ገትርን ለመከላከል እና የሚዝልስ (Measles) ክትባት ደግሞ ኩፍኝን (አንከሊስን) ለመከላከል የሚሰጡ ክትባቶች ናቸው። ሕፃናትን ከህመም፣ ከአካል ጉዳትና ከሞት ለመከላከል ወደ ክትባት መስጫ ማእከል መወሰድ ይኖርባቸዋል።
 • ያልተከተቡ ሕፃናት እንደ ሳምባ ነቀርሳ፣ ኩፍኝ፣ የሳንባ ምች፣ ማጅራት ገትር፣ ትክትክ፣ ዘጊ አናዳ፣ የልጅነት ልምሻና መንጋጋ ቆልፍ ያሉ በሽታዎች ሊይዟቸው ይችላሉ።
 • ከእነዚህ በሽታዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሕፃናትን የሚገድሉ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ለአካል ጉድለት የሚያደርሱ ናቸው።
 • እነዚህን በሽታዎች ክትባት በመውሰድ መከላከል ይቻላል።
ክትባትን የሚከለክል ሁኔታ የለም።
 • ክትባት ጉዳት ስለማያስከትል ለሁሉም ሕፃናት መስጠት ይቻላል።
 • ተቅማጥ፣ ሳልና ትኩሳት ያለባቸው ሕፃናት መከተብ ይችላሉ።
 • እነዚህን በሽታዎች ክትባት በመውሰድ መከላከል ይቻላል። ክትባትን ተከትሎ የሚመጡ ምልክቶች እንደ ትኩሳትና ጡት አልጠባም ማለት የተለመዱና ከ1 ቀን በላይ የማይቆዩ ናቸው።
 • ሕፃናት ሙሉ ክትባቶችን አንድ ዓመት ሳይሞላቸው መጨረስ ይኖርባቸዋል፤ አለበለዚያ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ አይሆንም።

የክትባት መርሀ ግብር

የተወለዱ እለት
 • ህፃናት እንደተወለዱ የኦፒቪ0 እና ቢሲጂ ክትባት ማግኘት ይኖርባቸዋል። አብዛኞቹ ጨቅላ ህፃናት በሳንባ ምችና በልምሻ የሚጠቁና ብሎም የሚሞቱ በመሆኑ በጠና ተቋም መውለድና ልጅሽ እነዚህን ክትባቶች እንዲያገኝ ማረግ ያንቺ ሃላፊነት ነው።
በ6ኛ ሳምንት
 • በተወለዱ በ 6ኛ ሳምንት አንቺም የድህረ ወሊድ የመጨረሻ ቀጠሮ የምታደርጊበት ቀን በመሆኑ ልጅሽን ለክትባት ይዘሽ መሄድ እንዳትዘነጊ። በዚህ ቀጠሮ ልጅሽ ኦፒቪ1 እና የፀረ አምስት (ዲፒቲ-ሄፕቢ-ሂብ1) ክትባትን ያገኛል። እነዚህ ክትባቶች ደግሞ የልጅነት ልምሻን፣ዘጊ አናዳ፣ ትክትክ፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ የጉበት በሽታ፣ የሳምባ ምችና ማጅራት ገትርን ለመከላከል ይረዳሉ።
በ10ኛ ሳምንት
 • በተወለዱ በ 10ኛ ሳምንት ሶስተኛ የክትባት ፕሮግራም ይኖራቸዋል። በዚህ ቀጠሮ ልጅሽ ኦፒቪ2 እና የፀረ አምስት (ዲፒቲ-ሄፕቢ-ሂብ2) ክትባትን ያገኛል። እነዚህ ክትባቶች የልጅነት ልምሻን፣ዘጊ አናዳ፣ ትክትክ፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ የጉበት በሽታ፣ የሳምባ ምችና ማጅራት ገትርን ለመከላከል ይረዳሉ።
በ14ኛ ሳምንት
 • ሶስተኛውን ክትባት ባደረጉ በወሩ የመጨረሻውን የኦፒቪ3 እና የፀረ አምስት (ዲፒቲ-ሄፕቢ-ሂብ3) ክትባትን ያገኛሉ። እነዚህ ክትባቶች የልጅነት ልምሻን፣ዘጊ አናዳ፣ ትክትክ፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ የጉበት በሽታ፣ የሳምባ ምችና ማጅራት ገትርን ለመከላከል ይረዳሉ።
በ9ኛ ወር
 • በመጨረሻው ቀጠሮም የሚዝልስ (Measles) ክትባት ኩፍኝን (አንከሊስን) ለመከላከል ይሰጣል።
 • የክትባትና የእድገት መከታተያ ካርዶችን በጥሩ ሁኔታ መያዝና፤ ወደ ጤና ተቋም በሄዱ ቁጥርም መውሰድ ያስፈልጋል።
 • Share on facebook
  Share on google
  Share on twitter

  አስተያየት

  መዝጊያ