ወባ

ወባ በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከሚባሉት የሕመምና የሞት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው። በሀገሪቱ መልክአ ምድር አቀማመጥና አየር ሁኔታ ምክንያት በኢትዮጵያ ወባ የሚተላለፍበት ሁኔታ ከቦታ ቦታና ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለዋወጣል። የዳበረ ተፈጥሯዊ የሰውነት መከላከያ ስለሌለ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በሙሉ በወባ ይጠቃሉ። ነገር ግን ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና እርጉዝ ሴቶች በወባ የመያዝ እድላቸውና በሽታው ሲይዛቸውም አስከፊ የመሆኑ እድል ከፍተኛ ነው፡፡ የወባ በሽታ መንስኤ የሚሆኑት ረቂቅ ተዋሲያን ሲሆኑ የሚተላለፉት አኖፊሌስ በምትባል ትንኝ አማካኝነት ነው። ይህች ትንኝ በውሃ ውስጥ ትራባለች።

ምልክቶች

አንድ ሰው በወባ ትንኝ ከተነከሰ ከ10 እስከ 14 ቀናት ውስጥ የወባ በሽታ ስሜቶችና ምልክቶች ይታያሉ
 • ራስ ምታት፣
 • ትኩሳት፣
 • ብርድ ብርድ ማለት፣
 • የመገጣጠሚያና የጡንቻ ህመም፣
 • ማላብ፣
 • የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣
 • ሳል (በሕፃናት ላይ)
 • ትውከትና ተቅማጥ
 • የደም ማነስ
 • በጣም ሲብስ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ ትውኪያ፣ ቅዥት፣ መንዘፍዘፍና ራስን መሳት፣ በጣም መድከም፣ የሰውነት መሟሸሽና የመተንፈስ ችግር ናቸው።

ማንን ያጠቃል

በወባ የመጠቃት እድል ከግልሰብ የጤና ሁኔታ ጋር የተያያዘ አደለም። ወባ ከምትኖሪበት አካባቢና ከወቅቱ ጋር ቁርኝት አለው። በወባ የመጠቃት እድል የሚጨምረው
 • የአየር ንብረት ለውጥ (የዝናብ መጠን፣ የሙቀት መጠንና የአየር እርጥበት) ሲጨምር
 • ግድቦችና መስኖዎች ካሉና በንፅህና ካልተያዙ
 • ወባ ያለበት አካባቢ እየኖሩ የፀረ ወባ የተነከረ አጎበር ውስጥ አለመተኛት
 • ወባ ያለበት አካባቢ እየኖሩ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ቤትን አለመርጨት

ህክምና

ወባ መታከም የሚችል በሽታ ቢሆንም ሳይፈጠር መከላከል ተመራጭ ነው። ለመከላከልም
 • ረግረጋማ ቦታዎችን ማድረቅ፣ ውሃ ማፋሰስ፣ ቦዮችን ማጽዳትና ገላጣ ማድረግ፣ በመስኖ ቦዮች ላይ የሚገኙ ሳሮችንና አረሞችን ማስወገድ
 • በፀረ ወባ ትንኝ መድኃኒት በተነከረ አጎበር ውስጥ መተኛት
 • ቤትን በየ6 ወሩ በፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ማስረጨት
 • በአካባቢ ቁጥጥር እርምጃዎች ሊወገዱ የማይችሉ የተጠራቀሙ ውሃዎች ሲኖሩ የፀረ ዕጭ ኬሚካል ርጭት በማካሄድ ውሃውን ማከም
 • ሆኖም ግን በበሽታው አንቺም ሆንሽ ልጅሽ ከተጠቃቹ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ይኖርባችኋል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ