የሚመከሩና የማይመከሩ ምግቦች

ምንም እንኳን የተመጣጠነ ምግብ ጤናችን ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅዎ ቢኖረውም አብዛኞቻችን ያገኘነውንና ስንበላው የሚጣፍጠንን ምግብ ብቻ እናዘወትራለን። በሀገራችን ያልተመጣጠነ ምግብ የመመገብ ዋነኛው ምክንያት ድህነት ወይም የምግብ ዕጥረት እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን በጣም ድሀ የሆነ ቤተሰብ እንኳን ገንዘቡን በብልሀት በመጠቀም የተሻለ መመገብ ይችላል። ሌላኛው በእርጉዞች ላይ የሚታየው ችግር ደግሞ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በባህልና ተለምዶ ተፅእኖ እርጉዝ ሴት አንዳንድ ምግቦችን እንዳትበላ የሚከለከል በመሆኑ ነው። እነዚህ የሚከለከሉ ምግቦች እንደየአካባቢው ቢለያዩም ስጋ፣ እንቁላል፣ ወተትና የወተት ተዋፅዎን እንዲሁም አታክልትና ፍራፍሬን ያጠቃልላሉ። በመሰረቱ ግን እነዚህ ምግቦች ለናትየውም ለልጇም በጣም አስፈላጊ ናቸው። በሶስተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚመጣው ማቅለሽለሽና ማስታወክ ሲሆን ይህን ተቋቁሞ ትንሽ ትንሽ ግን ቶሎ ቶሎ መብላት አስፈላጊ ነው። በአጠቃላይ እርጉዝ ሴቶች ከወትሮው አመጋገባቸው ከመቀነስ ይልቅ የበለጠ መጨመር እንደሚያስፈልጋቸው አምነሽ ተቀበይ።
Beautiful young blonde caucasian woman with pregnancy diet what to eat food guide

በእርግዝና ወቅት የሚያስፈልጉ ምግቦች

ሙቀትና ኃይል ሰጪ ምግቦች

ከገብስ፣ አጃ፣ ስንዴ፣ ጤፍና ማሽላ ከመሳሰሉ የጥራጥሬ ምግቦች እና ከእንሰትና ጎደሬ ከመሳሰሉት ከሥራ ስር ከሚዘጋጁ የምግብ ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡ እንደ ቂቤና ዘይት የመሳሰሰሉ ቅባትን የያዙ ምግቦችም ከፍተኛ ኃይል ሰጪ ናቸው፡፡

ሙቀትና ኃይል ሰጪ ምግቦች ለምን ያስፈልጋሉ?
 • አንቺም ፅንሱም በቂ ጉልበት እንድታገኙ ይረዳል፡፡
 • ተጨማሪ ጉልበት ስለሚያስፈልግሽ ከጥራጥሬ የተዘጋጁ ምግቦችን መመገብ አለብሽ፡፡
 • ከሦስተኛው የእርግዝና ወር ጀምሮ አንድ ተጨማሪ ምግብ በቀን መመገብ ይኖርብሻል፡፡ ይህም ለሚያስፈልግሽ ተጨማሪ ጉልበት፣ ክብደት ለመጨመርና ለጽንሱ በጣም አስፈላጊ ነው፤
 • ከሦስተኛው የእርግዝና ወር በኋላ አነስተኛ የሆነ የክብደት መጨመር ዘገምተኛ ለሆነ የፅንስ እድገት ያጋልጣል፡፡
 • ከስድስተኛው የእርግዝና ወር በኋላ የሚኖር ዝቅተኛ የክብደት መጨመር እናትየዋ ያለ ቀንዋ እንድትወልድ ሊያደርግ ይችላል፤
 • ኃይል ከመስጠት በተጨማሪ ቅባትነት ያላቸው ምግቦች ሰውነትሽ ቫይታሚን ‹‹ኤ››፣ ‹‹ዲ››፣ ‹‹ኢ›› እና ‹‹ኬ››ን እንዲጠቀም ይረዳሉ/ያግዛሉ፡፡
ሰውነት ገንቢ ምግቦች
ከእንስሳት ውጤቶች፡- ሥጋ፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ወተት፣ አይብና ዓሳ እንዲሁም ከእህል ዘሮች፡- አተር፣ ባቄላ፣ ምስር፣ ሽንብራ፣ አኩሪ አተርና የመሳሰሉት ገንቢ የምንላቸው ምግቦች ናቸው።
ሰውነት ገንቢ ምግቦች ለምን ያስፈልጋሉ?
 • ሰውነትን ፣ ጡንቻወችን፣ ቀይ የደም ሴሎችን፣ ፀጉርንና ሆርሞኖችን ለመጠገን እና ለመገንባት ይጠቅማሉ፤
 • የእንስሳት ውጤቶችና የእህል ዘሮችን ከተመገብሽ የጽንሱን ጤንነት ከመጠበቅ አልፎ ሰውነትሽ ለወሊድ ዝግጁ እንዲሆን እና ጡቷ እንዲያግት ይጠቅማል፡፡
በሽታ ተከላካይ ምግቦች
በቫይታሚንና በማእድን የበለጸጉ ምግቦች በሽታን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ የፍራፍሬና አትክልት ውጤቶች የሆኑት፡- ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ዱባ፣ ቡርቱካን፣ ስኳር-ድንች እና ካሮት እንዲሁም የእንስሳት ውጤቶች የሆኑት፡- ጉበት፣ ዘይት፣ ወተት እና እንቁላል በቫይታሚን የበለፀጉ ምግቦች ናቸው። በሌላ በኩል በውስጣቸው ካልሲየም የያዙ እንድ ወተት፣ የወተት ውጤቶች፤ ብረት የያዙ ቀይ ሥጋ፣ ጉበት፣ ልብ፣ ኩላሊት፣ ጥራጥሬ፣ አረንጓዴ ቅጠል ያላቸው አትክልቶችና አዮዲን የያዘ ጨው በሽታን ለመከላከል ይረዳሉ።
በሽታ ተከላካይ ምግቦች ለምን ያስፈልጋሉ?
 • ቫይታሚን ኤ በጨለማ ወቅት ማየት አለመቻልን ለመከላከልና በሽታን ለመቋቋም ይረዳል። የቫይታሚን ኤ እጥረትም በሕፃናት ላይ አይነስውርነትን ያስከትላል። በእርግዝናሽና ጡት በምታጠቢበት ወቅት በጣም ብዙ ቫይታሚን ኤ ያላቸው ምግቦችን መመገብ አለብሽ።
 • እያደገ ያለው ሕፃን በተለይ በእርግዝናው የመጨረሻ ጥቂት ወራት አዳዲስ አጥንቶች ለመስራት በጣም ብዙ ካልሺየም ያስፈልጉታል። አንቺም ጠንካራ አጥንትና ጥርስ እንዲኖርሽ ካልሺየም ያስፈልግሻል።
 • ብረት ደምን ጤነኛ ለማድረግና የደም ማነስን ለመከላከል ይረዳል። በቂ ኃይል እንዲኖርሽ፣ በወሊድ ጊዜ ብዙ ደም እንዳይፈስሽ ለመከላከል፣ እና እያደገ ያለው ሕፃን ጤናማ ደም እንዲኖረውና ከተወለደ በኋላ ላሉት ጥቂት ወራትም የሚያስፈልገውን ያህል ብረት ይዞ እንዲወለድ ለማስቻል በጣም ብዙ ብረት ያስፈልግሻል።
 • አዮዲን ላንቺ እንቅርትን (የአንገት ላይ እብጠትን)ና ሌሎች ችግሮችን ይከላከልልሻል። የአይዲን እጥረት ያለባት እርጉዝ ሴት ሕፃን ልጇ የአእምሮ ዝግመት ኖሮበት እንዲወለድ ማለትም በጣም የከፋ የአእምሮና የአካል ጉድለት ይዞ እንዲወለድ ሊያደርገው ይችላል።
ውሃ

ሰውነት ጤናማ እንዲሆን፣ ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በሰውነትሽ ውስጥ በማዘዋወር እና ሰውነትሽ የማያስፈልገውን ቆሻሻ ለማስወገድ ይጠቅማል ለዛም በቂ የሆነ ውሃ መጠጣት ይኖርብሻል (በቀን ከ8-10 ኩባያ)።
 • በእርግዝና ወቅት ክብደት ክትትል ያስፈልግሻል፡፡ በ 9 ወር ውስጥ ቢያንስ 9 ኪሎ መጨመር አለብሽ፡፡ ነገር ግን እርጉዝ ከመሆንሽ በፊት የነበረሽ ክብደትን አማክሎ መጨመር ያለብሽ ክብደት ከፍ ሊል ይችላል። አብዛኛዎቹ ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት ከ 11ኪግ-16ኪግ ክብደት ይጨምራሉ። በመጀመሪያዎቹ 3 ወራቶች ውስጥ ከ 1-2ኪሎ መጨመር ሲመከር የተቀረውን የእርግዝና ጊዜ በሳምንት ከ0.25-0.5ኪሎ እንድትጨምሪ ይመከራል።

በእርግዝና ወቅት የማይወሰዱ ምግቦች

ምንም እንኳን በእርግዝና ወቅት የሚበሉ ነገሮች ብለን የዘረዘርናቸው ምግቦች ሁሉንም የሚያጠቃልሉ ቢመስሉም መበላት የሌለባቸውና በእርግዝና ወቅት የማይመከሩ ምግቦች አሉ። ከነዚህም ውስጥ
 • ጥሬ ስጋና አሳ
 • ያልበሰለ አትክልትና ፍራፍሬ
 • ጥሬ እንቁላል
 • ጣፋጭና (በተፈጥሮ የሆኑትን ሳይጨምር)ጨው የበዛባቸው ምግቦች
 • አልኮል ቡናና ሻይ መጠጣት: አልኮል በፍፁም የተከለከለ ሲሆን የሻይ ወይም የቡና ሱስ ካለብሽና ካስቸገረሽ ከአንድ ሲኒ በላይ እንዳትወስጂ።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ