የአራስ ልጅ እንክብካቤ

ለአዲስ ጨቅላ ሕፃን የሚከናወኑ አስፈላጊ ተግባራት ከተወለደበት ደቂቃ ጀምሮ የሚሰጥና በጣም አስፈላጊ እንክብካቤ ነው። እነዚህን እንክብካቤዎች ሙሉ በሙሉ ለመስጠት በህክምና ተቋም መውለድ ተገቢ ነው። አንድ ጨቅላ ህፃን እንደተወለደ:
 • ሕፃኑን ማድረቅና እንዲተነፍስ ማነቃቃት – ሕፃኑ የማይተነፍስ ከሆነ አፉንና አፍንጫውን በንጹሕ ጨርቅ ማጽዳት (የሃኪም ባለሙያ መሆንን ይጠይቃል)
 • የሕፃኑን አተነፋፈስና ቀለሙን መመርመር (ከ60 በላይ በደቂቃ ውስጥ መተንፈስ እና ቀለሙ ቢጫ መሆን አደገኛ ምልክቶች ናቸው)
 • እትብቱን በደንብ ቋጥሮ መቁረጥ
 • ሕፃኑን ከመወለዱ ካንቺ ጋር ገላ ለገላ እንዲነካካ (እንዲተቃቀፍ) አድርጎ ማስተኛት
 • ወዲያውኑ ጡት ማጥባት መጀመርና ከጡት ውጪ ምንም አይነት ነገር አለመስጠት(ውሃንም ጨምሮ)
 • ጭኑ መሀል ላይ (በፊት ለፊት በኩል) 1 ሚ.ግ ቫይታሚን ኬ መውጋት (የሃኪም ባለሙያ መሆንን ይጠይቃል)
 • ክብደቱን መለካት (የሃኪም ባለሙያ መሆንን ይጠይቃል)
 • ሃኪምን ሳታማክሪ ምንም አይነት ባህላዊ ተግባራትን አለማድረግ።

ያንቺ ግዴታዎች

ጡት ማጥባት እንዳለ ሆኖ (ስለጡት ማጥባት አስፈላጊነት የተብራራ መረጃውን አንብቢ) ለልጅሽ ልታደርጊው የምትችይው ዋና ዋና እንክብካቤ

ሙቀት መስጠት

አዲስ የተወለዱ ሕፃናትን በአብዛኛው ቅዝቃዜ የሚያገኛቸው ከተወለዱ በኋላ በሚኖሩት የመጀመሪያ 5 ደቂቃዎች ውስጥ ነው። አዲስ የተወለዱ ሕፃናት የሰውነት ሙቀታቸውን እንደ አዋቂ መቆጣጠር ስለማይችሉ ከቅዝቃዜ ሊጠበቁ ይገባል። ጨቅላ ሕፃናት ሙቀት እንዲያገኙ የሚከናወኑ ተግባራት
 • ሕፃናቱ የተወለዱበትንና የሚቆዩበትን ቦታ ሙቀት እንዲኖረው ማድረግ (ቦታው ግን በጭስ እንዳይታፈን ማድረግ)
 • ወዲያው እንደተወለዱ (ከማኅፀን እንደወጡ) ሕፃናቱን ማድረቅ። የረጠበውን ጨርቅ ወይም መታቀፊያ ቀይሮ በሌላ ደረቅ ጨርቅ (መታቀፊያ) መቀየር እና መጠቅለል
 • ሕፃኑ እና እናቱ ገላ ለገላ ተነካክተው እንዲተኙ ማድረግና ሁለቱንም በደረቅ የአልጋ ልብስ ወይም ብርድ ልብስ መጠቅለል
 • ለሕፃኑ ቆብ ማጥለቅና ካልሲ (የእግር ሹራብ) ማድረግ
 • አንቺ ለማጥባትና ሕፃኑ ለመጥባት ዝግጁ እንደሆናቹ ወዲያውኑ እንደወለድሽ (ቢዘገይ በአንድ ሰዓት ውስጥ) ጡት ማጥባት መጀመር
 • ሕፃኑን በተወለደበት ቀን አለማጠብ (ቢቻል እስከ ሶስት ቀን መጠበቅ)፤ ሲታጠብ ለብ ባለ ውሃ ማጠብ

እትብቱን መንከባከብ

በተለምዶ ቁስልን ያድናሉ ብለን የምናስባቸውን ነገሮች እትብቱን ለማድረቅ መሞከር አይመከርም። ለእትብት እንዲደረግ የሚመከር እንክብካቤ
 • የሕፃኑን እትብት ከመንካት በፊት እጅን በደንብ መታጠብ
 • የሕፃኑን እትብት ሁልጊዜም ንጹሕና ደረቅ ማድረግ። የሕፃኑን እትብት ምንም ነገር አለመቀባት።
 • ዳይፐር ወይም ሽንት ጨርቅ ስታስሪ ከእትብቱ በታች ማሰር
 • የሕፃኑ እትብት መድማት አለመድማቱን ተመልከች። እየደማ ከሆነ ቋጠሮው ላልቶ እንደሆነ ተመልከቺ ከላላ በደንብ መቋጠር።
 • የኢንፌክሽን ምልክት እንደ መሽተት፣ መቅላት፣ መግል ማውጣትና የሰውነት ሙቀት መጨመር ምልክቶች ካሳየ ሕፃኑን ወደ ጤና ተቋም ወዲያውኑ ውሰጂ።
✸ አስታውሺ: እትብቱን ምንም ነገር መቀባት (እበት፣ቅቤና ሌሎች ነገሮችን)፤ ደሙን በሳሙናና በውሃ ማጽዳት፤ የእትብቱን ቋጠሮ ማላላት፤እትብቱን በራሱ መቋጠር፤ እትብቱን በፕላስተርና በጨርቅ ማሸግ፤ እትብቱን በንጹህ ዓመድ መደምደምም ሆነ በጨርቅ መተኮስ ፍፁም የተከለከለ ነው።

ንፅህናን መጠበቅ

ጨቅላ ህፃናት ተወልደው 24 ሰአት ሳይሞላቸው ገላቸውን ማጠብ ለሳምባ በሽታ ተጋላጭነታቸውን ስለሚጨምር ቢቻል እስከ ሶስት ቀን አለማጠብ ይመረጣል። መጣጠብ ሲጀምሩም በሳምንት ሁለቴ ከታጠቡ በቂ ነው። ይህም ቆዳቸው እንዳይደርቅ ይረዳል። ማጠብ ከመጀመርሽ በፊት የሚያስፈልጉ ነገርችን በሙሉ አዘጋጂ። የእትብት ቋጠሯቸው እራሱ እስኪላቀቅ ድረስ ገላቸውን ሲታጠቡ እትብቱን ውሃ እንዳይነካው መጠንቀቅ አለብሽ። የምትጠቀሚው ውሃ በውጨኛው መዳፍሽ ስትነኪው ምቅ የሚል መሆን አለበት። ሴት ከሆነች መራቢያ አካላቷን ስታጥቢ ሳሙና መጠቀም የለብሽም። ቢቻል ከማጠብ በንፁ ጨርቅ ውሃ አስነክቶ መጥረግ ይመከራል። ወፍራም ከሆኑና የተጣጠፈ ሰውነት ካላቸው እነፃን ቦታዎች እየከፈትሽ ማጠብ ይኖርብሻል። እነዚህ እጥፋቶች ባልተፀዱ ቁጥር የቆዳ መቆጣትን ያመጣሉ። አጥበሽ ከጨረሽም በኋላ ቅባት ባትቀቢ ይመረጣል። የልጆች ቆዳ ጠንካራ ስላልሆነ ቅባት መቀባት ሽፍታን ሊያስከትል ይችላል። ልጅሽን ለሰከንድም ቢሆን ውሃ ውስጥ ጥለሽ እንዳትሄጂ።
የሽንት ጨርቅ ስትቀይሪም ንፁህና እጥብ በሆነ ጨርቅ ጠርገሽ ተቀያሪ ሽንት ጨርቅ ከማድረግሽ በፊት ንፋስ እንዲነካቸውና እርጥበቱ እንዲደርቅ ይሁን። ይህ ሽፍታ እንዳይከሰት ይረዳል። ሴት ልጅን ስታፀጂና ስትጠርጊ ሁሌም ከብልቷ ወደመቀመጫዋ ጥረጊ ይህም ቆሻሻ ወደውስጧ እንዳይገባና ያደርጋል። ሰውነታቸውን ስለማይቆጣጠሩና እራሳቸውን ሊቧጭሩ ስለሚችሉ ሁሌም ጥፍራቸው መቆረጥ አለበት። አይናቸውና ጆሮአቸው በየቀኑ መፀዳት ስላለበት በለስላሳና በረጠበ ጨርቅ ማፅዳት ይኖርብሻል። ስታፀጂም ከላይ ከላይ ብቻ መሆን አለበት፤ በፍፁም ጅሮ፣ አይንና አፍንጫ ውስጥ እንዳትገቢ።

ግርዛት

ወንድ ልጅች ከተወለዱ 7 ቀን ከሞላቸው መገረዝ ይችላሉ። ከተገረዙ በኋላ ህመም ስለሚኖረው ልጅሽን በደንብ መንከባከብ ይኖርብሻል። ጡት ከማጥባት ባለፈ ንፅህናውን በንፁ ውሃ ብቻ በማጠብ መጠበቅ ያስፈልጋል። ሽንትጨርቅ ከማልበስ በፊትም መድረቁን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ከ 5 እስከ 7 ወን ውስጥ ይድናል ነገር ግን
 • ደም የሚፈሰው ከሆነ
 • ተገርዞ እስከ 10 ሰአት ባለው ውስጥ ሽንቱን ካልሸና
 • የኢንፌክሽን ምልክት እንደ ማበጥ፣ መሽተት፣ መቅላትና ፍሳሽ ማውጣት ከጀመረ
 • ሙቀቱ ቀጨመረ፤ ተቅማት ካለው፤ ምግብና እንቅስቃሴ ላይ ከተዳከመ ባፋጣኝ ወደ ሃኪም ውሰጂው

ልጁ/ጅቷ በጣም ዝቅተኛ ክብደት ካለው/ላት

ክብደታቸው ትንሽ ለሆኑ ሕፃናት ክብደታቸው ትንሽ የሆኑ ሕፃናት አስፈላጊው እንክብካቤ ከተደረገላቸው ከፍተኛ የሆነ የመኖር እድል አላቸው፡፡ የሚከተሉት ችግሮች ክብደታቸው ትንሽ የሆኑ ሕፃናት ላይ የሚከሰቱ ናቸው፡-
 • በቀላሉ ይቀዘቅዛሉ፣
 • ጡት ለመጥባት ይቸገራሉ፣
 • በበሽታ በቀላሉ ይጠቃሉ፣
 • የመተንፈስ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ክብደታቸው ትንሽ የሆኑ ሕፃናት በሁለት በጣም ዝቅተኛና ዝቅተኛ ተብለው ይከፈላሉ። በጣም ዝቅተኛ (ከ1,500 ግራም በታች የሆነ) ክብደት ያላቸው ህፃናት የመተንፈስ ችግሮች ስላሉባቸውና መጥባት ሊያቅታቸው ስለሚችል ሆስፒታል መቆየት ይኖርባቸዋል። ዝቅጠኛ (1,500 – 2,500)ክብደት ያላቸው ልጆች ከሆኑ
 • ጡት ቶሎ ቶሎ ማጥባት፣ ቢያንስ በየሁለት ሰዓቱ ቀንና ማታ፣
 • ጡት በደንብ የማይስቡ ከሆነ የታለበ የእናት ጡት ወተት በኩባያ/ማንኪያ መስጠት፣
 • ሙቀት በደንብ እንዲያገኙ ተጨማሪ እንክብካቤ ማድረግ፣ ይህን ለማድረግ ጥሩ የሆነው አማራጭ ከእናት ጋር ገላ ለገላ እንዲገናኙ ማድረግ ነው፣
 • በበሽታ ቶሎ ስለሚጠቁ ለንጽህና ትኩረት መስጠት፣
 • ተከታታይ እና ተጨማሪ የድህረ ወሊድ ክትትል ማድረግ: ይህ የልጁን እድገት ለመከታተልና ተጨማሪ/አማራጨ እንክብካቤ እንዲያገኝ/ድታገኝ ይረዳል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ