ጡት ማጥባት ችግሮች

ጡት ማጥባትን ከሚያከላክሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ የጡት ህመም ነው። በተለይ የመጀመርያ ልጅ ላይ ጡት ማጥባት አዳጋች ሊሆን ይችላል። የተለመዱ የጡት ማጥባት ችግሮችንና መፍትሄዎቹን ከዚህ በታች ታገኛለሽ።

  በቂ የእናት ጡት ወተት አለመኖር

  የችግሩ መንስኤዎች
  • ዘግይቶ ጡት ማጥባት መጀመር፣
  • ልጁ ጡቱን በደንብ ጨርሶ እንዲጠባ አለማድረግ፣
  • ቶሎ ቶሎ አለማጥባት፣ ከጡት ወተት ሌላ ፈሳሽ መስጠት፣
  • ጡቱን በትክክል አለማጉረስና ሕፃኑ/ኗን በትክክል አለመታቀፍ
  መከላከያ ዘዴዎች
  • ቀንም ሌሊትም ጡት ብቻ ማጥባት፣
  • ሕፃኑ በፈለገ ሰዓት ሁሉ ቀንም ሌሊትም ማጥባት ቢያንስ 10 – 12 ጊዜ፣
  • ጡቱን በትክክል ማጉረስና ሕፃኑ/ኗን በደንብ መታቀፍ
  • ለሕፃኑ/ኗ ሁለተኛውን ጡት ከማጥባትዎ በፊት የመጀመሪያውን ጡት እስኪጨርሱ መጠበቅ
  መፍትሔዎች
  • ረፍት ማድረግ፣ ብዙ ፈሳሽ መጠጣት፣
  • ሕፃኑ በፈለገ ቁጥር ማጥባት እያዳንዱን ጡት ህጻኑ እስከቻለ ድረስ ማጥባት፣
  • ሌላ ተጨማሪ ነገር (ውሃ፣ የዱቄት ወተት፣ ሻይ፣ ወይም ፈሳሽ) ለህፀኑ መስጠት ማቆም፣
  • ጡቱን ለህፃኑ በስርአቱ ማጉረስ

  የጡት ማበጥ (በጣም ብዙ ወተት ማጋት)

  ሁለቱንም ጡት የሚያጠቃ ሲሆን የሞላ፣ የሚሞቅ እና የሚያም ጡት እና መለስተኛ የቆዳ መቆጣት (መቅላት)ምልክቶችን ያሳያል።

  የችግሩ መንስኤዎች
  • ጡት ማጥባት ዘግይቶ መጀመር፣
  • በተደጋጋሚ አለማጥባት፣ ጡቱን በትክክል አለማጉረስ፣
  • ጡቶቹን ሙሉ በሙሉ አጥብቶ አለመጨረስ፣
  መከላከያ ዘዴዎች
  • አስተቃቀፍና የጡት አጎራረስን ማስተካከል
  • ሕፃኑ እንደተወለደ ወዲያው ጡት ማጥባት፣
  • ሕፃኑ ጡት በፈለገ ሰዓት ሁሉ (ሕፃኑ የፈለገውን ያህል በተደጋጋሚና መጥባት እስኪያቆሙ ድረስ) እና ቀንም ሌሊትም ማጥባት፣
  • ለሕፃኑ ሁለተኛውን ጡት ከማጥባትዎ በፊት የመጀመሪያውን ጡት እስኪጨርስ መጠበቅ፣
  መፍትሔዎች
  • ሕፃኑ/ኗ በደንብ ጡቱን መሳብ ከቻለ/ች ቶሎ ቶሎ ማጥባትና በትክክል ማቀፍ
  • ሕፃኑ/ኗ መጉረስ ካልቻለ/ች ለብ ባለ ውሃ የተነከረ ፎጣ/ጨርቅ/ ጡቱ ላይ ማስቀመጥና ከላይ ወደጡቱ ጫፍ በቀስታ ማሸትና የጡቱን ጫፍ የከበበው ጥቁሩ ክፍል እስኪላላ ድረስ ጥቂት ወተት እንዲፈስ ማድረግ እና የጡት አጎራረሱ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠሽ ሕፃኑ/ኗ እንዲጠባ/እንድትጠባ ማድረግ፣
  • ጠባብ ልብስ አለመልበስ፣ ጡት ካጠባሽ በኋላ የጡቱን እብጠትና ህመም ለመቀነስ በቀዝቃዛ ውሃ (በበረዶ) በተነከረ ፎጣ ጥትሽን ጫን ጫን ማድረግ፣

  የሚያም (የቆሰለ) የጡት ጫፍ

  የጡቱ ጫፍ የቆሠለ ወይም የተሰነጠቀ ሆኖ አልፎ አልፎ ሊደማ ይችላል። የችግሩ መንስኤዎች
  • በደንብ ጡቱን ጎርሶ መያዝ አለመቻል ወይም ምቹ ያልሆነ አስተቃቀፍ
  መከላከያ ዘዴዎች
  • ሕፃኑን በትክክል ይዞ (አቅፎ) ማጥባት እና ጡትን በትክክለኛው መንገድ ማጉረስ፣
  • ጡጦ አለመስጠት
  • የጡት ጫፍን አለማጠብ (በተለይ በተደጋጋሚ እና በሣሙና አለማጠብ)፣
  መፍትሔዎች
  • አስተቃቀፍሽን ማስተካከል
  • ማጥባት ስትጨርሺ ትንሽ ወተት በጡትሽ ጫፍ ላይ ማድረግ (ይህ የጡቱን ጫፍ ያለሰልሰዋል) እና በንፋስ ማድረቅ፣
  • ጡትሽን ስትታጠቢ ሳሙና አለመጠቀም፣ እንዲሁም የጡቱን ጫፍ ምንም ዓይነት ቅባት አለመቀባት
  • ጡት ማጥባትሽን ቀጥይ፤ እያፈራረቅሽ በጣም የማያምሽን ጡት ማጥባት፣

  የተዘጉ የወተት መውረጃ ቧንቧዎች እና የጡት እረት (መቆጣት)

  የጠጠረ እና በጣም የሚያም፣የጠጠረው ቦታ ለብቻው በጣም የቀላ እና የተቆጣ፣የሰውነት ትኩሳት፣ እና ከጡት ውጪም ህመም መሰማት ምልክቶቹ ናቸው።

  የችግሩ መንስኤዎች
  • ጣቶችሽን በመቀስ ቅርጽ አርገሽ ጡትን መያዝ፤
  • ጠባብ ልብሶችን መልበስ፣
  • በአብዛኛው በደረት በኩል መተኛት፣
  መከላከያ ዘዴዎች
  • ሰፋፊ ልብሶችን መልበስና በደረት መተኛትን ማስቀረት
  መፍትሔዎች
  • ማጥባት ከመጀመርሽ በፊት ህመም ባለበት የጡቱ ክፍል ላይ በሞቀ ውሃ የተነከረ ጨርቅ ተጠቅሞ በቀስታ ማሸት፣
  • እረፍት ማድረግና ብዙ ፈሳሽ መውሰድ
  • ጠባብ ልብስ አለመልበስ፣
  • የበለጠ በተደጋጋሚ ማጥባት፣
  • የኢንፌክሽን ምልክቶች ከታዩብሽ ወደ ጤና ጣቢያ መሄድ
  Share on facebook
  Share on google
  Share on twitter

  አስተያየት

  መዝጊያ