ያለግዜው መውለድ

ያለ ጊዜው መውለድ ወይም የምጥ ቀድሞ መምጣት ማለት በእርግዝና ወቅት ሠውነት መውለድ ካለበት ግዜ ቀደም ብሎ ዝግጁ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ምጥ ቀደሞ መጣ የሚባለው መውለድ ካለብሽ ጊዜ ከ 3 ሳምንት በፊት ቀድሞ ከጀመረሽ ነው፡፡ የቅድመ ወሊድ ክትትል የምታደርጊ ከሆነ ሃኪምሽ በተቻለ መጠን ልጁ እድገቱን ጨርሶ እንዲወጣ ለማገዝ መውለጃሽ እንዲዘገይ ያደርጋል። ይህም ልጅሽ እድገቱን በአንቺ ውስጥ ሆኖ እሰከመውለጃሽ ቀን ድረስ ከቆየና በትክክለኛው ጊዜ ከተወለደ ከወሊድ በኋላ ሊያጋጥም የሚችሉ ችግሮችን ለመቀነስ ይረዳዋል፡፡

ምልክቶች

ያለጊዜሽ ላለመውለድ የሚታዩሽን ምልክቶች በአግባቡ መከታተል አለብሽ ፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ምልክቶች 37 ሳምንት ሳይሆንሽ ከታዩብሽ ወደ ጤና ጣቢያ በአስቸኳይ መሄድ ወይም ሀኪም በተቻለ አቅም ሊያይሽ ይገባል።
 • የጀርባ ህመም ፡- ከጀርባሽ የታችኛው ክፍል የሚሠማሽ ሲሆን ህመሙም ተከታታይ ወይም መጣ ሔደት የሚልና ቦታ ብትቀይሪ ምቾትሽን ብታስተካክዪ እንኳን የማይተው
 • በየ 10 ደቂቃው ወይም ቶሎ ቶሎ የሚሰማ የመቁረጥ ስሜት
 • በወር አበባሽ ጊዜ የሚሰማሽ አይነት ቁርጠት ሲሰማሽ
 • ከብልትሽ የሚወጣ ፈሳሽ
 • ብልትሽ አካባቢ ግፊቶችን ከጨመሩ ወይም ፅንሱ ወደታች እየገፋ እንደሆነ የሚሰማ ስሜት
 • ማቅለሽለሽ ፤ ማስመለስ ወይም ማስቀመጥ
 • የደም መፍሰስ

ማንን ያጠቃል

በተለያዩ ምክንያቶች ያለጊዜው ለሚመጣ ምጥ ተጋላጭ ልትሆኚ ትችያለሽ ፡፡ ከነዚህም ውስጥ
 • ሲጋራ ማጨስ
 • ከእርግዝና በፊት ከልክ ያለፈ ውፍረት ወይም ዝቅተኛ ክብደት ከነበረ
 • የቅድመ ወሊድ ክትትል አለማድረግ
 • በእርግዝና ግዜ አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም
 • የጤና ችግር ፡- ለምሳሌ የደም ግፊት ፤ ስኳር፤ የደም መጓጎል ችግር ወይም ኢንፌክሽን
 • ፅንሱ የጤና ችግር ከነበረበት / ካለበት
 • ሁለትና ከዛ በላይ ፅንስ መሸከም
 • በቤተሰብሽ ውስጥ ያለጊዜው የሚመጣ ምጥ ያጋጠመው ሰው ካለ
 • ከወለድሽ በኋላ ወዲያው በድጋሚ ከተረገዘ

ህክምና

ያለግዜው ምጥሽ ከመጣ በኋላ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ከመፈጠሩ በፊት መከላከል አማራጭ ነው። ያለጊዜው የሚመጣን ምጥ ለመከላከል
 • የቅድመ ወሊድ ክትትልሽን በስርአቱ ማድረግ
 • የስኳርና የደም ግፊት ካለብሽ ህክምናን መከታተልና ችግር እንዳያመጡ መቆጣጠር
 • መጠጥ፤ ሲጋራና የመሳሰሉትን አደንዛዥ ነገሮች አለመጠቀም
 • የተመጣጠነ ምግብ መብላት
 • ክብደት ከመጠን በላይ አለመጨመርም ከሚያስፈልገው በታችም አለመሆን
 • ኢንፌክሽን ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን ከራስሽ ማራቅ
 • ጭንቀትን መቀነስ
 • ነገር ግን ይህን ማረግ ባትችይና ምጥሽ ከ 37 ሳምንት በፊት ከመጣ ያለጊዜአቸው የሚወለዱ ህፃናትን መንከባከብያ (ማሞቅያ) ያለበት ሆስፒታል መውለድ ይኖርብሻል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ