ድህረ ወሊድ

የድኅረ ወሊድ እንክብካቤ ከወሊድ ጀምሮ ለ6 ሳምንታት ያህል ለእናትየዋና ለሕፃኑ/ኗ የሚሰጥ እንክብካቤ ነው። የድህረ ወሊድ እንክብካቤ አስፈላጊ የሆነው፣

 • ምንም ችግር ለሌለባቸው እናትና ሕፃን ስለሚሰጥ እንክብካቤና ስለተዛማጅ የጤና ችግሮች ለማማከር፣
 • እናትየዋንና ሕፃኑን የጤና ችግር እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ቀድሞ ለማወቅ እና ለመመርመር
 • ለማናቸውም ዓይነት የጤና ችግር ቀድሞ እንክብካቤ ለመስጠት
 • ከወሊድ በኋላ እርግዝናን ለመከላከል ስለሚረዱ መንገዶችና መፍትሄዎች ለማማከርና አገልግሎት ለመስጠት ነው።

በአጠቃላይ የድኅረ ወሊድ እንክብካቤ፤ አጠቃላይ የጤና ሁኔታን በተመለከተ ምርመራ ማድረግ፣ የጤና ትምህርት መስጠትና አጠቃላይ የጤና እንክብካቤ መስጠትን ያጠቃልላል። የመጀመርያው የድህረ
ወሊድ ቀጠሮ በመጀመርያው 24 ሰአት ውስጥ መሆን ሲኖርበት ከሱ በተጨማሪ በወለድሽ በ 3ኛ ቀን፤ በ 7ኛ ቀንና 6ኛ ሳምንት ሌሎች የድህረ ወሊድ ክትትሎች ይኖሩሻል።

የድህረ ወሊድ ቀጠሮዎች

በመጀመርያው 24 ሰአት ውስጥ የምታገኝው የድህረ ወሊድ እንክብካቤ ላንቺም ለልጅሽም በሂዎት መቀጠል በጣም ወሳኝ ነው። ከወለድ ጋር ተያይዞና ከወሊድ በኋላ ባሉ 24 ሰአት ውስጥ የሚከሰቱ የጤና እክሎች ለብዙ እናቶችና ህፃናት ሞት ምክንያት ነውና ሁሌም በጤና ተቋም ውለጂ። በተለያዩ አጋጣሚውች በህክምና ተቋም ካልወለድሽ በወለድሽ በ24 ሰአት ውስት ወደ ሃኪም መሄድ ይኖርብሻል። ተከታታይ ቀጠሮዎችንም በአግባቡ መከታተል ይኖርብሻል። በድህረ ወሊድ ክትትል ወቅት
 • አንቺና ልጅሽ ሙሉ የጤና ምርመራ ይደረግላችኋል፤ የሚሰማሽ ህመም ወይም ሌላ ችግር ካለ ትጠየቂያለሽ
 • አንቺና ልጅሽ አደገኛ የሚባሉት ምልክቶች እንዳሉባቹና እንደሌሉባቹ ይታያል፡- ካሉባቹ ተገቢው ህክምና ይሰጣል
 • ያንቺንና የልጅሽን ሂዎት አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ አደገኛ ምልክቶች ትምርት ይሰጣል
 • የመንጋጋ ቆልፍ ክትባትና፣ የቫይታሚን ኤ እንክብል ይሰጥሻል
 • የአይረን እንክብል ወስደሽ ካልጨረሰች እንድትቀጥይ ይነገርሻል (በአጠቃላይ ለ6ወር ያህል መውሰድ ይኖርብሻል)
 • ከወሊድ በኋላ ሊደረጉ ስለሚገቡ እንክብካቤዎች:-ስለ አመጋገብ ሁኔታ፣ የንጽህና አጠባበቅ፣ ስለአጎበር አጠቃቀም፣ ጤናማ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለግል ንጽህና፣ ስለ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ምክር ይሰጣል
 • በመጀመርያው ቀጠሮ ልጅሽ የፖልዮ (Polio) እና ቢ.ሲ.ጂ BCG ክትባት ያገኛል
 • ከልጅሽ ጋር ተያይዞ ስለ ጡት ማጥባት፤ ለእትብት የሚደረግ ጥንቃቄ፤ ሙቀት አጠባበቅ፤ ንጽህና አጠባበቅ እና የክትባት ጥቅም ትረጃለሽ
 • ከመጀመርያው ቀጠሮ በኋላ ባሉ ቀጠሮዎች ጡት ማጥባት ችግር ካለ መፍትሄ/ህክምና ይሰጣል፤ በምጥም ወለድሽ በቀዶ ጥገና ሰውነትሽ ማገገሙ ይታያል፤ ልጅሽ ክብደት መጨመር አለመጭመሩ ይለካል
 • በመጨረሻው ቀጠሮ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ግንዛቤ በመፍጠር ፍቃደኛ ከሆንሽ የመረጥሽውን አገልግሎት ታገኛለሽ
 • በያንዳንዱ ቀጠሮ ቀጥሎ ስለሚኖርሽ የድህረ ወሊድ ቀጠሮ ይነገርሻል

አደገኛ ምልክቶች

ከወሊድ በኋላ በነብሰጡር እናቶች ላይ ሊታዩ የሚችሉትን አደገኛ ምልክቶች ማወቅ ባፋጣኝ ወደህክምና ተቋም ለመሄድ ይረዳሉ። ከሶስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት የእናቶች ሞት በወሊድና ከወሊድ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናቶች የሚከሰት በመሆኑ ይህን ጊዜ በጥንቃቄ ማሳለፍ ይኖርብሻል። የወሊድ ተፈጥሮአዊ ሂደት በራሱ ሰውነትሽን ላደጋ ስለሚያጋልጥ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት አደገኛ ምልክቶች ውስጥ አንዱም እንኳን ከታየብሽ ባፋጣኝ ህክምናን መሻት ይኖርብሻል
 • ከማህጸን የደም መፍሰስ (ብዙና ድንገት መጠኑ ሲጨምር)፡- ከወሊድ በኋላ የወር አበባ መጠን ያለው የደም መፍሰስ ክስተት ጤናማ ነው። ከወሊድ በኋላ ባሉት ቀናት እየቀነሰና የፈሳሹ ቀለምም ቀይነቱ እየቀነሰ ይሄዳል። ነገር ግን ብዙ ደም እየፈሰሰሽ ከሆነና በቀን ብዙ ጊዜ ጨርቅ (ፓድ) መቀየር ካለብሽ
 • ትኩሳት (የሰውነት የሙቀት መጠን ≥38 ዲ.ሴ. ከሆነ)፡- ትኩሳት የመመረዝ ምልክት ነው
 • በታችኛው የሆድ ክፍል የሚሰማ ከባድ ህመም፡- ደም በማኅፀን ውስጥ እየፈሰሰ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል
 • ከባድ ራስ ምታት/ብዥ ያለ እይታ እና መንዘፍዘፍ/ራስን መሳት፡- የእናትየዋ የደም ግፊት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ያመለክታል
 • መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ ከብልት መፍሰስ፡- የመመረዝ ምልክት ነው
 • በባት ላይ የሚሰማ ከፍተኛ ህመም – እብጠት ኖረውም አልኖረውም፡- በደም ቧንቧ ውስጥ የደም መርጋት ምልክት ሊሆን ስለሚችል አደገኛ ነው። ወደ ከፍተኛ የጤና ተቋም ወዲያውኑ መሄድና በምትጓጓዥበት ጊዜም እግርሽ ከዳሌሽ በላይ ወደላይ ከፍ ማለት አለበት። ያበጠውም ቦታ መታሸት የለበትም።
 • ራስሽን ወይም ልጅሽን ልትጎጂ እንደምትችይ የሚሰማሽ ከሆነና፤ የሌለ ነገር ይታይሽ ከጀመረ፡- ሕይወትን የሚያሰጋ የአእምሮ ህመም ምልክት በመሆኑ ወዲያውኑ ወደ ከፍተኛ የጤና ተቋም መሄድ አለብሽ።
እነዚህ ምልክቶች ታዩብሽም አልታዩብሽም የድህረ ወሊድ ክትትል ማድረግ ይኖርብሻል።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ