ጡት ማጥባት

እንደ እናት ከምታደርጊያቸው ወሳኝ የመጀመሪያ ውሳኔዎች መካከል ልጅሽን ምን መመገብ እንዳለብሽ የምትወስኚው ውሳኔ አንደኛው ነው። የጤና ከፍተኛ ባለሙያዎች እና ሐኪሞች ከልጅሽ ዕድሜ ለመጀመሪያዎቹ 6 ወራት የእናት ጡት ወተት ብቻ እንድትሰጪ አበክረው ይመክራሉ። ከ6 ወር በኋላ ልጅሽ ተጨማሪ ምግብ መጀመር ሲኖርበት ከተጨማሪ ምግቡ ጋር አብሮ የናት ጡት ሁለት አመት እስኪሆነው እንዲያገኝ ይመከራል። ለዛም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የጡት ማጥባት ባህሪያት እንዲኖሩሽ ያስፈልጋል። ጡት ማጥባት ላንቺና ለልጅሽ የሚሰጠውንም ጥቅም ጠንቅቀሽ አንብቢ።
 • በመጀመሪያ የሚወጣውን ቢጫ መልክ ያለውን የጡትሽን ወተት አዲስ ለተወለደው ሕጻን አጥቢ፡፡ ከምግብነቱ በተጨማሪ በሽታን እንዲቋቋም ይረዳዋል፡፡ ይህ ቢጫ ወተት (እንገር) የተፈጥሮ ቅቤ ስላለው ከሕጻኑ ሆድ ጥቁር አይነምድር በቶሎ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ አዲስ የተወለደው ሕጻንም በበሽታ እንዳይጠቃ የሚያግዙ ንጥረ-ነገሮች የያዘ ነው፡፡ እንገር የመጀመሪያው የተፈጥሮ ክትባት ነው፡፡
 • በወሊድ ሰአት ልጅሽን እንደተገላገልሽ ወዲያውኑ ጡት ማጥባት ጀምሪ፡፡ የእንግዴ ልጁ እስኪወጣ መጠበቅ አይኖርብሽም፡፡ ይህም ጡትዎ ቶሎ ወተት እንዲያግት ያደርጋል፡፡ ጡት ወዲያውኑ (ሕፃኑ በተወለደ በመጀመሪያ አንድ ሰዓት) ውስጥ ማጥባት የእንግዴ ልጁ በቶሎ እንዲወጣ በማድረግ የደም መፍሰስን ይቀንሳል፡፡ ከጡት ወተት በፊት የሚሰጡ እንደ ውሃ፤ ውሃ በስኳር እና ቅቤ ማዋጥ የመሳሰሉ ነገሮች አላስፈላጊ እና ጎጂ ናቸው፡፡ በተጨማሪ በመጀመሪያዎቹ ቀኖች በቂ የጡት ወተት እንዳይመነጭ ያደርጋል፡፡
 • ልጅሽ ስድስት ወር እስኪሞላት ድረስ ጡትሽን ብቻ አጥቢያት፡፡ ውሃም ቢሆን አትስጪ፡፡ ጠንካራና ጤናማ ልጅ ይኖርሻል፡፡ ጡትን ብቻ ማጥባት ልጅሽ ምርጥ እና የዳበረ ምግብ እንድታገኝ ከማድረጉ በተጨማሪ የተቅማጥና የመተንፈሻ አካል ህመም እንዳይዛት ይከላከላል፡፡ ልጅሽን ውሃና ሌሎች ፈሳሽ መስጠት በተቅማጥ በሽታ እንድትጠቃ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ሆዷ በውሃ ስለሚሞላ ጡት የመጥባት ፍላጎቷ ይቀንሳል፡፡ ክብደትም አትጨምርም፡፡ የጡት ወተት እስከ ስድስት ወር ላለ ሕጻን የውሃ ጥማቱን ለማርካት የሚሆን በቂ ውሃ አለው፤ በጣም ሞቃታማ ወቅትም ቢሆን፡፡
 • ልጅሽ ጡት መጥባት በፈለገ ጊዜ ሁሉ አጥቢው፡፡ ቀንና ሌሊትን ጨምሮ ከ10-12 ጊዜ ማጥባት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ካደረግሽ ጡትሽ በደንብ ያግታል፤ ሕጻኑም በቂ ወተት ያገኛል፤ የተስተካከለ እድገት ይኖረዋል፤ ጤናማም ይሆናል፡፡ ቶሎ ቶሎ ማጥባት ጡት በደንብ እንዲያግትና ወተቱም እንዲፈስ ያደርጋል፤ በእናትና በሕጻን መካከል ደግሞ የጠነከረ ፍቅር እንዲመሰረት ይረዳል፡፡ ጡት ስታጠቢ ሕጻኗ በተገቢው መንገድ መታቀፏንና ጡትሽን በሚገባ መጉረሷን አረጋግጪ፡፡ ይህም በቂ ወተት እንድታገኝ ከማድረጉ በተጨማሪ የጡት ጫፍ መቁሰል መሰነጣጠቅና ሌሎች የጡት ችግሮችንም ያስወግዳል፡፡
 • ማጥባት የጀመርሽውንን አንደኛውን ጡት ወተቱ እስከ ሚሟጠጥ ድረስ አጥቢ፡፤ ከዚያም ወደ ሌላው አዛውሪ፡፡ ይህም ሕፃኑ ወደኋላ የሚመጣውን በምግብ የዳበረውን የጡት ወተት ለማግኘት ያስችለዋል፡፡ ሕፃኑ ሲጠባ በመጀመሪያ የሚያገኘው ውሃ የበዛበትን ወተት ነው፤ ይህም ጥሙን ለማርካት ያስችለዋል፡፡ ከበስተኋላ የሚመጣው ወተት ግን በምግብነቱ የዳበረ የሚያጠግብ ነው፡፡ ይህ ረሀቡን ያስታግስለታል፤ ይህን ከጠባ ብዙ ማልቀስና መነጫነጭ አይታይበትም፡፡
 • ያንቺም የሕጻኗም ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን ጡት ስታጠቢ ከወትሮው በተጨማሪ ሁለት ጊዜ ምግብ መመገብ ይኖርብሻል፡፡ ጡት የሚያጠቡ እናቶች ጤንነታቸው የተስተካከለ እና በቂ ወተት እንዲያግቱ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ወትሮ ከሚመገቡት በተጨማሪ መመገብ አለባቸው፡፡
 • የአባላዘር በሽታ ካለባት
 • ልጅሽ ከታመመ ጡትሽን ቶሎ ቶሎ አጥቢው፡፡ በአጭር ጊዜ እንዲድን ያግዘዋል፡፡ ልጅሽ ስለታመመ ጡት ማጥባት ማቋረጥ የለብሽም፡፡ በተለይ ተቅማጥ ከያዘው በተቻለ መጠን ቶሎ ቶሎ ይጥባ፤ ከሰውነቱ የሚወጣውን ፈሳሽ ይተካለታልና፡፡ ጡት ማጥባት መቀጠሉ ሕጻኑ ክብደት እንዳይቀንስ፤ በሽታን እንዲቋቋም፤ ምቾትና መረጋጋት እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ልጅሽ ብቻ ሳይሆን አንቺም ብትታመሚ ጡት ማጥባት መቀጠል ትችያለሽ፡፡
 • ልጅሽ ከህመሟ ካገገመችም በኋላ ቶሎ ቶሎ ጡት ስጫት፡፡ ጤንነቷና ክብደቷ በፍጥነት እንዲመለስ ይረዳታል፡፡ ብዙ ሕፃናት ሲያማቸው ክብደታቸው ይቀንሳል፡፡ ስለዚህም ክብደታቸው በአጭር ጊዜ እንዲመለስ ጡት ቶሎ ቶሎ መጥባት አለባቸው፡፡
በተጨማሪም ጡት ስታተቢ አስተቃቀፍሽና ጡት አጎራረሱ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሻል። ትክክለኛው የአራስ ልጅ አስተቃቀፍ
 • የሕፃኑ ጭንቅላትና ሰውነት ቀጥ ያለ (አንገቱ ካልተጠማዘዘ)፣
 • ሕፃኑ ወደ እናቱ ገላ ተጠግቶ የታቀፈ፣
 • ሕፃኑ በጡቱ ትይዩ (ፊት ለፊት) የሆነ፣
 • የሕፃኑ ሙሉ ሰውነት በደንብ ተደግፎ የተያዘ ነው
ትክክለኛ ጡት አጎራረስ ደግሞ
 • የጡት ጫፍ ላይ የሚገኘው ጥቁሩ ከፍል ከሕፃኑ/ኗ አፍ በታች ሳይሆን በላይ በብዛት ከታየ፣
 • የሕፃኑ/ኗ አፍ በደንብ ከተከፈተ፣
 • የታችኛው ከንፈሩ/ሯ ወደውጪ ከተገለበጠ፣
 • አገጩ/ጯ ጡቱን ከነካ ሕፃኑ/ኗ ጡቱን በደንብ ጎርሷል/ሳለች ማለት ነው።
Share on facebook
Share on google
Share on twitter

አስተያየት

መዝጊያ